በአማራ ክልል ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸው ተገለጸ።
በአማራ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን ለመግለጽ የተጠሩ ሕዝባዊ ሰልፎች ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።
በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መከላከያ ሠራዊት ለሀገር አንድነት፣ ለሕዝቦች ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ለኅብረ ብሔራዊነት መረጋገጥ የከፈለውና እየከፈለ ያለውን የላቀ መስዋዕትነት በታላቅ ክብር መዘከራቸው ተገልጿል።
ሰልፎቹ በሰላም፣ በድምቀትና ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቁ የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሕዝቡን ከጎኑ አድርጎ በሰፊ ቅንጅት እና በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት መስራቱ ጉልህ ሚና እንደነበረው ተመላክቷል።
የሕዝቡ የላቀ ትብብርና የሕግ አክባሪነት ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን አስችሏል።
የጸጥታ አካላት ሕዝቡ ለሰላም፣ ለሕግ የበላይነት እና ለሀገር ደኅንነት ላደረገው ሰፊ ትብብርና አጋርነት ምስጋና አቅርበው ህብረተሰቡ የተጀመረውን የሰላም ግንባታ እና የጸጥታ አስተማማኝነት በጋራ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።


