12ኛው የጣና ፎረም ጉባኤን በማስመልከት በባህር ዳር ከተማ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ እና አማራጭ መንገዶች ይፋ ተደረጉ።
ጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2019 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የሚታደሙ የክብር እንግዶችን አቀባበል እና ሽኝት ቅልጥፍና ለማረጋገጥ ከኤርፖርት እስከ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ያለው ዋና መንገድ ለተሽከርካሪዎች ዝግ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ገለጹ።
ኮማንደር ዋለልኝ እንደገለጹት ህብረተሰቡ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና አሽከርካሪዎች መደበኛ የእለት ተእለት እንቅስቃሴአቸው እንዳይስተጓጎል እና የትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚከተሉትን አማራጭ መንገዶች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፦
ከአባይ ማዶ በሚመጡ አሽከርካሪዎች፦ በአሮጌው ድልድይ አድርገው በሚመጡበት ወቅት የአልማ ወተር ፍሮንት መስመርን መጠቀም ይችላሉ።
ከመሀል ከተማ ወደ ገጠር መንገድ ለሚንቀሳቀሱ፦ በአዝዋ አድርገው ወደ ሙሉ ዓለም፣ በሰርፀ ጀርባ ቀጥታ ወደ 6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ በሚያስወጣው ዋና የኮብልስቶን መንገድ በማለፍ፣ የድሮውን አልካን አቋርጠው ወደ ሀይሌ ትምህርት ቤት እና ቀጥታ ወደ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ ይችላሉ።
ከገጠር መንገድ ተነስተው ወደ ከተማ ለሚገቡ፦ በጎፋ ካቶሊክ ሆስፒታል በኩል አድርገው ዲፖን በመቁረጥ ወደ ኪዳነ ምህረት መስመር መጠቀም የሚችሉ ይሆናል።
በኤርፖርት መስመር ለሚንቀሳቀሱ፦ ዋናውን የተባበሩት እና ሰራፂዮን ማርያም መስመርን በመጠቀም በኢላ ማደያ አድርጎ በማርዳ እብነ-በረድ 40 ሜትር አስፓልት ወደ ዋናው መስመር መግባት ይቻላል።
በተጨማሪም የኤርፖርት ታክሲዎች ጊዜያዊ ማቆሚያ (ፌርማታ) ለፓርኪንግ ተብሎ በተዘጋጀው በአልማ ወተር ፍሮንት መንገድ ላይ የተዘጋጀ መሆኑን የፖሊስ መምሪያ አዛዡ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ጉባኤው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባሉት ቀናት በጣና ሀይቅ ላይ ምንም አይነት የጀልባ እንቅስቃሴ የማይኖር በመሆኑ የወደብ አካባቢ ማህበረሰብ፣ የጀልባ አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው አሳስበዋል።


