በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋለውን የትራፊክ አደጋ ስጋት በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
ህፃናት እና ተማሪዎች ከቤት ወደ ትምህርት ቤት በሚያደርጉት ጉዞ ከትራፊክ አደጋ ሰለባነት ለመጠበቅ የሚያስችል አራማጅና አስተማሪ አሰራር በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
የአደጋውን አስከፊነት ለመቀነስ ከንድፈ-ሃሳብ ግንዛቤ እስከ አጋዥ የተማሪ ትራፊክ ማደራጀት ሰፊ የንቅናቄ ስራ እየተሰራ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል ።
በንጉስ ተክለሃይማኖት ክፍለ ከተማ የ4ተኛ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክፍል ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አበባው አየለ እንደገለጹት፣ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚታዩ የትራፊክ ስጋቶችን በመለየት ተማሪዎች በዕውቀት እንዲጠበቁ ሰፊ የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የትራፊክ ምንነትን፣ የአደጋውን አስከፊነትና መንስኤዎች፣ ትክክለኛ የመንገድ አጠቃቀም ስልቶችን እንዲሁም አደጋን ለመከላከል የሚወሰዱቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን አስመልክቶ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል።
ከንድፈ-ሃሳባዊ ትምህርቱ ባሻገር፣ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲተማመኑ እና መንገዱን በደህንነት እንዲያቋርጡ የሚያግዙ ቡድኖችን የማደራጀት እና የምዝገባ ስራዎች በስፋት እየተካሄዱ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
ይህ አበረታችና አርአያነት ያለው ስራ በክፍለ ከተማው በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ እንዲሆን በዘመቻ መልክ እየተሰራ ይገኛል።
ህብረተሰቡን እና ትምህርት ቤቶችን አስተባብሮ የሰውን ህይወት ለመታደግ የተጀመረው ጅምር ለሌሎች አካባቢዎችም ምርጥ ተሞክሮ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተጠቁሟል።



