የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የ119ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሠራዊት 119ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ለመላው የሠራዊቱ አባላትና አመራሮች የተሰማውን ጥልቅ ደስታና ክብር እየገለጸ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ዋና ጠቅላይ መምሪያው ባስተላለፈው መልዕክት የመከላከያ ሠራዊታችን የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የድንበር ደህንነትና ሕልውና በማስከበር ረገድ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ የጻፈ፣ የኢትዮጵያ ጽናትና የነጻነት ምሰሶ መሆኑን ገልጿል።
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ሌት ተቀን ያለዕረፍት እየከፈለ ያለው ታላቅ መስዋዕትነት፣ አርበኝነትና ጀግንነት በኢትዮጵያ ሕዝብና ታሪክ ዘወትር የሚታወስ መሆኑ ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በመልዕክቱ አያይዞም የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሕዝብን ሰላም ለማፅናትና የሀገርን ፀጥታ ለመጠበቅ ከቀን ወደ ቀን ከሚጠናከረው የመከላከያ ሠራዊት ጎን ሁሌም በጽናት እንደሚቆም አረጋግጧል።
በመጨረሻም ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሰላም ሲባል በየዕለቱ የሚከፈለው መስዋዕትነት ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የጸጥታ ኃይል ልጆቹን በክብር ያመሰግናል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።


