የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የላቀ አፈጻጸም ላላቸው አባላቱ እውቅና ሰጠ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በስራ አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የመሰረታዊ ፖሊስ ስልጠና ኢንስቲትዩት አባላት የማበረታቻ ሽልማትና የዕውቅና ሰርተፊኬት አበረከተ።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሸነር አበበ ደለለ እንደገለጹት ሽልማቱ አባላቱ ለቀጣይ ተልዕኮዎች በበለጠ ተነሳሽነትና ውጤታማነት እንዲሰሩ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ምክትል ኮሚሸነር አበበ አክለውም የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን አመራሮችና አባላት የማበረታታትና እውቅና የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሽልማቱን የተቀበሉት የፖሊስ አባላት በበኩላቸው የተሰጣቸው እውቅና በቀጣይ ተቋማዊ ተልዕኮዎችን በአግባቡ ለማከናወን የሚያነቃቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ መኮንኖች ተገኝተዋል።







