በደብረ ብርሃን በህዝባዊ አደረጃጀት ወንጀልን የመከላከል ስራ ውጤት ማመጣቱ ተገለጸ።
የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ከከተማው ፖሊስ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ባቋቋሙት የብሎክ አደረጃጀት የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ማስጠበቅ መቻላቸውን ገለጹ።
የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አባይ ሙሉነህ እንደገለጹት፤ በከተማዋ 311 ብሎኮች በንቃት ተደራጅተው መረጃና ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ህዝባዊ አደረጃጀቱ ቀደም ሲል ይፈጸሙ የነበሩ የዘረፋ፣ የስርቆት እና መሰል ወንጀሎችን በመቀነስ ረገድ አወንታዊ ለውጥ ማምጣቱንም ኮማንደር አባይ አክለው አብራርተዋል።
በጠባሴ ክፍለ ከተማ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቀበሌ ፖሊስ ኦፊሰር ሳጅን ጌታሁን አሽኔ በበኩላቸው ማህበረሰቡ ያሳየው ንቁ ተሳትፎ በተለይም በምሽት ከስራ በሚመለሱ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ላይ ይፈጸም የነበረውን የስልክ መቀማት፣ የስርቆትና የድብደባ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነሱ ማድረጉን ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በአደረጃጀቱ አማካኝነት የእገታና የስርቆት ወንጀሎች መቀነሳቸውንና አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ጠቅሰው ከእነሱ አቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም ለፀጥታ ኃይሉ ጥቆማ በመስጠት እየተባበሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አጋርነትን ይበልጥ ለማጠናከር አደረጃጀቱን አሰፍቶ የማስቀጠል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።






