በኮምቦልቻ ከተማ የወንጀል መከላከልን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የሚያስችል የስልጠና መድረክ ተጀመረ።

በኮምቦልቻ ከተማ የወንጀል መከላከልን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የሚያስችል የስልጠና መድረክ ተጀመረ።

የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ እና የፖሊስን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም በማጎልበት ወንጀልን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የስልጠና መድረክ በወሎ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ተጀመረ።

ስልጠናው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የለማውን “AFP APP” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ሶፍትዌር አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሲሆን በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ እና በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙህዬ እንደገለጹት መተግበሪያው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ወንጀልን በቅርበት ለመከታተል፣ መረጃዎችን በፍጥነት ለመተንተን እና የቅኝት ስራዎችን በብቃት ለማከናወን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የቴክኖሎጂ መምሪያ ተወካይ ኢንስፔክተር አበበ ወንዴ በበኩላቸው የመተግበሪያው ዋና አላማ የህዝብ ተሳትፎን በማሳደግ የሚሰበሰቡ ጥቆማዎችን ወደ ሚስጥራዊ እና ስልታዊ ማስረጃነት መቀየር እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ ኢንስፔክተር አበበ ማብራሪያ፣ ይህ ቴክኖሎጂ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ማንነታቸው ሳይጋለጥ ወንጀሎችንና አደጋዎችን በቀጥታ ለፖሊስ እንዲያደርሱ፤ የንብረታቸውን ደህንነት እና የቀረቡ ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ እንዲከታተሉ፤ ለተላከው መረጃ ፈጣን ምላሽ ካልተሰጠም አሰራሩን ተከትለው ቅሬታ እንዲያቀርቡ የሚያስችል አሰራር ያለው ነው።

በተጨማሪም ለፖሊስ አመራሮች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት እና የተሳለጠ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል የሁኔታ ትንተና ለማዘጋጀት እንደሚረዳ ተመላክቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መተግበሪያው ፖሊስ ከባህላዊ የመረጃ አሰባሰብ ወደ ዘመናዊና ቴክኖሎጂ መር አሰራር እንዲሸጋገር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top