3,460 የክላሽንኮቭ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ መነሻውን በማድረግ ወደ ወልድያ ከተማ ህገ-ወጥ ጥይቶችን ጭኖ ለማስገባት የተደረገ ሙከራ በህዝብና በጸጥታ አካላት ጥምር ርምጃ መክሸፉን ፖሊስ ተገለጸ።
ኮማንደር አበራ ካሳው የወልድያ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እንደገለጹት ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ.ም. ከቆቦ ከተማ ተነስተው በኮድ-3-14122 አአ ታርጋ ቁጥር ባጃጅ ተሽከርካሪ ላይ ከዕቃ ጋር ሻግ በማዘጋጀት እና መሸፈኛ የእንስሳ መኖ በማልበስ ተተኳሹን ለማዘዋወር ተሞክሮ ነበር።
እንደ ኮማንደር አበራ ገለጻ ተሽከርካሪው ወልድያ ከተማ ሲገባ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሰጠው ጠቃሚ ጥቆማ መሰረት በራያ በር (ዳቦ ቤት) ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በዚህም በህገ-ወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ የነበሩ 3,460 የክላሽንኮቭ ተተኳሺ ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ አዛዡ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሎች እያደረገ ያለው እገዛ የህግ ማስከበር ስራውን ውጤታማ እንዳደረገው የገለጹት ኮማንደር አበራ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።



