በባህር ዳር ከ14 ሺህ 600 ሊትር በላይ ህገ-ወጥ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ14 ሺህ 600 ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የኢኮኖሚና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ፈለቀ ታሪኩ እንደገለጹት ነዳጁ በቁጥጥር ስር የዋለው መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ሰባታሚት ቀበሌ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት በተደረገ ክትትል ነው።
በተደረገው ፍተሻም በ73 በርሚል የተቀዳ በጥቅሉ ከ14 ሺህ 600 ሊትር በላይ ህገ-ወጥ ነዳጅ መያዝ ተችሏል ሲሉ ነው ኢንስፔክተር ፈለቀ ያብራሩት።
ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የአንድ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው አስፈላጊው የምርመራ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቁመዋል።
ኢንስፔክተር ፈለቀ አክለውም ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር የሀገርን ኢኮኖሚ ከማናጋቱም በላይ በህብረተሰቡና በፀጥታ ኃይሉ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያበላሽ በመሆኑ ችግሩን በጋራ መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመጨረሻም የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችና በህገ-ወጥ ድርጊቱ የሚሳተፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያስጠነቀቁት ኢንስፔክተሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም ህገ-ወጥነትን የመታገል ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።




