“ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የነጻነታችን እና የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ምልክት ነው!” ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ
“ሰንደቅ ዓላማችን ለሕብረ ብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች፣ የአማራ ክልል ፖሊስ አመራሮችና አባላት፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ምክር ቤት የጽሕፈት ቤት ሰራተኞች ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ማርች ባንድ ወታደራዊና ሀገራዊ ይዘት ያላቸውን ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎች በማቅረብ ሁነቱን አድምቆታል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነታችን፣ የነጻነታችን እና የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ምልክት ነው ብለዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር በቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የተከፈለውን መስዋዕትነት እያሰብን፣ የሀገራችንን አንድነት እና የህዝቦቻችንን አብሮነት በሚያጠናክር መንገድ ሊሆን ይገባል ሲሉ አክለዋል።
ሰንደቅ ዓላማ ለሕብረ ብሔራዊ መግባባት እና ለዘላቂ ሰላም መሠረት እንዲሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበር በተለይም በክልላችን ደረጃ በሕግ ማስከበርና በፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ የተሰማሩ የጸጥታ ኃይሎቻችንን የሀገር ፍቅር፣ የሙያ ቁርጠኝነት እና መስዋዕትነት የምናጎላበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የፀጥታ አካላቱ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ እያከናወኑት ያለው ተግባር የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ የማስቀል ያህል ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) አጉልተው አብራርተዋል።
ይህ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሉ ደረጃ በሕግ ማስከበርና በፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ የተሰማሩ የጸጥታ ኃይሎችን የሀገር ፍቅርና የሙያ ቁርጠኝነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑ ተመላክቷል።












