የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት የሰላምና ልማት ትብብር ማህበር የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ገመገመ።
የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት የሰላምና ልማት ትብብር ማህበር የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄደ።
በውይይቱ ላይ የማጠቃለያ ሪፖርት ያቀረቡት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው እንደገለጹት በመመሪያው መሰረት ክፍያ ለሚያስፈልጋቸው የማህበሩ አባላት እና ለቤተሰቦቻቸው ዘላቂ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ለመስጠት ከተመሰረተበት ከሐምሌ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህም በማህበሩ የ15 ዓመታት ጉዞ እስካሁን ከ3,380 በላይ ለሚሆኑ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ያመለከቱት ረዳት ኮሚሽነር አብዮት በባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ9.8 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት የፖሊስ አባላት በፍቃደኝነት ማህበሩን የመቀላቀል ፍላጎታቸው ማደጉ የማህበሩን ካፒታልና የድጋፍ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገው ተመልክቷል።
አሰራርን ለማዘመንና ግልጽነትን ለማስፈን ሲባል የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ በእጅ ንክኪ አልባ (ከባንክ ወደ ባንክ በሚደረጉ ትራንዛክሽኖች) እንዲከናወኑ መደረጉ እና የመረጃ አያያዝን ለማሻሻል መረጃዎችን በአንድ ቋት የማደራጀት ስራ መጀመሩ በጠንካራ ጎን ተነስቷል።
በሌላ በኩል የመረጃ አያያዝን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ዘዴ በማደራጀት የአባላቱን ቁጥርና የማህበሩን ካፒታል የበለጠ ማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ የቦርድ አባላቱ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በበኩላቸው የማህበሩን የወደፊት የስራ አቅጣጫዎች፣ የአሰራር ማሻሻያዎችን እና የቀጣይ ጉባኤ ዝግጅቶችን አስመልክተው ዋና ዋና መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
በዚህም የማህበሩ የሂሳብ አሰራር በውጭ ኦዲት እንዲሁም በመንግስት ኦዲተሮች አማካኝነት በግልጽነት ተፈትሾ ስራ ላይ እንዲውል እንደሚደረግና የክፍያ እና የመረጃ መመዝገቢያ ስርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ አሳስበዋል።
በማጠቃለያውም የማህበሩን አሰራሮች የበለጠ ውጤታማና ተቋማዊ ለማድረግ በቦርድ አባላቱ የተነሱ ጥቆማዎችን ጨምሮ የተበታተኑ ስራዎችን የሚያስተካክሉ አዳዲስ መመሪያዎች በዕቅዱ ላይ ተካተው ስራ ላይ እንደሚውሉ ተገልጿል።





