17 የህገወጥ ታጣቂ ቡድን አባላት በታች አርማጭሆ ወረዳ እጅ ሰጡ።
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በወርቅ ምድር እና በኩርቢ ቀበሌዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ ቡድን አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጡ።
በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የነበረውን ስብስብ በመምራት ላይ የነበረው ሙሉ አቸነፍን ጨምሮ 17 የቡድኑ አባላት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በምህረት እጃቸውን መስጠታቸውን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።
እጃቸውን የሰጡት የቡድኑ አባላት 1 ኤም-14 ጠመንጃ፣ 8 የክላሽ ንኮቭ መሣሪያዎች፣ 2 የቃታ መሣሪያዎች እና ልዩ ልዩ ጥይቶችን ይዘው ገብተዋል።
የወረዳው ፖሊስ እንደገለጹት የተቀሩት የህገወጥ ታጣቂ ቡድን አባላትም የሰላሙን አማራጭ ተቀብለው እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በአካባቢው ሙሉ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለው አስታውቀዋል።



