መጪው የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ-ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መጪው የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን የቅድመ-ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንዳሉት መጪውን የመስቀል በዓል በሰላም ለማጠናቀቅ የፀጥታ ግብረ-ሃይል በማቋቋም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ወንጀሎች ከተፈጠሩ ወንጀለኞችን ተከታትሎ በመያዝ እና ምርመራ በማጣራት ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ግብረ-ሀይል መቋቋሙንም ጠቁመዋል።
በበዓላት ወቅት ህገ-ወጥ የጥይት ተኩስን ጨምሮ ርችት መተኮስም ሆነ ሌሎች ህገወጥ ተግባራት በጥብቅ የተከለከሉ መሆኑን የጠቆሙት አዛዡ ከሚፈነዱ እና ተቀጣጣይ ከሆኑ ነገሮች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሁሉም ዞኖች የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ በማድረግ በዓሉ ከደመራ እስከ ፍፃሜ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጂት መደረጉን ያመላከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትም አስፈላጊው ስራ ይሰራል ሲሉ ገልፀዋል።
በበዓላት ወቅት የሚፈጠሩ የስርቆት፣ ማጭበርበር እና ሌሎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ የፀጥታ መዋቅሩ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ ራሱን ከማንኛውም አደጋ በመከላከልና ወንጀሎች ሲፈፀሙ በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት በዓሉን ማክበር እንደሚገባም ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጥሪ አቅርበዋል።


