በባህርዳር ከተማ የሚደረጉ ስፖርታዊና ልዩ ልዩ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የቅድመ ዝግጂት ስራ መሰራቱን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ ዓለም ዓቀፍ ስታድየም የሚደረገውን የኢትዮጵያና የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን የእግር ኳስ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ዝግጅት ማደረጉን በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ገለፃ ስፖርታዊ ውድድሩ ከውድድርነት ያለፈ የሁለቱ ሀገራትን መልካም ግንኙነት የሚያሳድግ በመሆኑ በሰላም እንዲጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
ሰርጎ ገብነትን፣ ህገ-ወጥነትን እና ሰላምን የሚያውኩ ማናቸውንም ተግባራት ቀድሞ ለመከላከል የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የተጠናከረ ስራ ለመስራት መዘጋጀቱንም ነው አዛዡ የተናገሩት።
ከሁለቱ ሀገራት የስፖርት ውድድር በተጨማሪም በባህርዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ያለምንም ስጋት እንዲጠናቀቁ የሚያስችል ዝግጂት ስለመኖሩም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ጠቁመዋል።
ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው ስፖርታዊ ውድድሩን ለመታደም የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎች ያለምንም ስጋት እንዲከታተሉ የሚያስችሉ የፍተሻ፣ የአካባቢ ጥበቃና የስጋት ቀጠናዎችን ቀድሞ በመለየት የመጠበቅ ስራና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል ብለዋል።
የከተማዋ ፖሊስ ከመደበኛ ተግባሩ ጎን ለጎን የሁነቱን በሰላም መጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከተውም ኮማንደር ዋለልኝ አክለዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብ የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት እሴቱን በመላበስ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ሚናውን እንዲወጣም አዛዦቹ ጥሪ አቅርበዋል።





