የጽናት መሰረቱ የህዝብና የሀገር ፍቅር እንዲሁም ሙያዊ ብቃት መሆኑ ተገለፀ።

የጽናት መሰረቱ የህዝብና የሀገር ፍቅር እንዲሁም ሙያዊ ብቃት መሆኑ ተገለፀ።

የአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር አባላትና አመራሮች በተገኙበት የጳጉሜን 3 ‘የፅናት ቀን’ “ፅኑ መሠረት ለማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በታላቅ ድምቀት በፓናል ውይይትና በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ተከብሯል።

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ‘የፅናት ቀንን’ አስመልክቶ ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ ኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥቷን በጽናት እየገነባች መሆኑን አብራርተዋል።

ዕለቱ ሀገር የመጠበቅና የመከላከል ዓቅምን ለማሳየት፣ የፀጥታ ተቋማትን ዘመናዊ ቁመና ለማጎልበትና ለሀገረ-መንግሥቱ ዘላቂነትና ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ክብር ለመስጠት ያለመ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ያለ ፅኑነት ትልቁን ሀገራዊ ስኬት ማሳካት እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ቀኑ ለጸጥታ መዋቅሩና ለሰራዊቱ መሰጠቱ ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጸው ሀገርን ለማጽናትና ህልውናን ለማስቀጠል የጸጥታ ኃይሉ የከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነትና ያሳየውን የፅናት ተምሳሌትነት አድንቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ውስብስብ የደህንነት ስጋቶችንና የመፍረስ አደጋዎችን በጽናት በመቋቋም የክልሉን ሰላም መመለስ መቻሉን ያብራሩት አስተባባሪው በአሁኑ ወቅትም አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲፋጠኑ ለማድረግ የፖሊስ፣ የማረሚያ ቤት፣ ሚሊሻና የደጀን ኃይል ተቋማዊ የሪፎርም እና የግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣይም የህዝቡን ሙሉ ነፃ እንቅስቃሴና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም የጸጥታ አካላት በጥብቅ ቅንጅት የመምራትና የተጋረጡ ስጋቶችን የመቀልበስ ስራ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው የጽናት መሰረቱ የህዝብና የሀገር ፍቅር እንዲሁም ሙያዊ ብቃት መሆኑን ገልጸዋል።

የጸጥታ አካላት ለለበሱት ዩኒፎርም፣ ለህዝብና ለሀገር ባንዲራ ታማኝ መሆን እንደሚገባቸው ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ አሳስበዋል።

ጽናትን ለማጎልበት ሙያን ለተሰጠ ዓላማና ሀገራዊ ግዴታ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ አባላቱ በአሁኑ ተቋማዊና ሀገራዊ ሁኔታ ተስፋ ሳያቆርጡ፣ የታሪክና የማህበረሰብ እሴቶችን መሰረት በማድረግ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በጽናትና በጀግንነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፅናት ለኛ ውርሳችን፣ ርስታችንና የማንነታችን መገለጫ ነው በማለት፣ ፅናት የሚመጣው ከሀገር ወዳድነት፣ ለህገ-መንግስቱና ለህዝብ እፎይታ ዋጋ ከመክፈል እንዲሁም ህገ-ወጥነትና ሴራን ከመጸየፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጸጥታ አካላቱ በጥብቅ ቅንጅት መስራታቸው ክልሉን ከነበረበት የጸጥታ ስጋት ወጥቶ ወደ ብርሃንና ሰላም እንዲሸጋገር ማድረጉን ያመላከቱት ኃላፊው፤ የመንግስት መዋቅር እንዳይፈርስ ማድረግ መቻሉን፣ የጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዕለቱ በተካሄደው የፓናል ውይይት የተሳተፉ የጸጥታ መዋቅሩ አባላትና አመራሮች በሰጡት አስተያየት የተመዘገቡ የሰላም ፍሬዎች የጋራ መተጋገዝና የጠንካራ ቅንጅት ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይም ይህን የመተማመን፣ የፅናት እና የተቋማዊ ግንባታ ጉዞ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top