“ፅናት ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል ውድ ዋጋ ነው!!” አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)
በአማራ ክልል የጸጥታ ተቋማት ትብብር የጳጉሜን 3 የፅናት ቀንን ‘ፅኑ መሠረት ለማንሰራራት’ በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች እየተከበረ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከሌሎች የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም የሚከበረውን ‘የፅናት ቀን’ በጋራ በማክበር ላይ ይገኛሉ።
በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ የዕለቱ ክብር እንግዳ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ፣ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አቶ አስቻለው አላምሬ የሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት ተገኝተዋል።
የዕለቱ ክብር እንግዳ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት “ፅናት ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል ውድ ዋጋ ነው” ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት ሀገራዊ እና ክልላዊ ተልዕኳቸውን በመወጣት ረገድ እያሳዩት ያለው የፀና አቋምና ተጋድሎ ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች ትስስራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የእለቱን መረሃ-ግብር አስመልከቶ የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ለውይይት የሚሆን መነሻ ጽሁፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በሚካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የክልሉ የጸጥታ ተቋማት በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር በተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ወደፊት በሚከናወኑ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያካሂዱ ታውቋል።
ይህ ‘የፅናት ቀን’ አከባበር የጸጥታ ተቋማቱን የተቀናጀ ህዝባዊ አገልግሎትና ዝግጁነት የበለጠ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ተቋማቱ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት መድረክ መሆኑ ተገልጿል።














