የልጃገረዶች ክብረ በዓላት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።
በአማራ ክልል ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በልዩ ድምቀት ሲከበሩ የቆዩት ባህላዊ የልጃገረዶች ክብረ በዓላት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።
የቡሄ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ፣ ከሴ አጨዳ እና አሱሪቴ በዓላትን በአንድ አደባባይ የሚያሰባስበው ይህ ታላቅ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር እሁድ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:00 ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ስቴዲዮም ይካሄዳል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በዓሉ በሰላም እና በፍፁም ደህንነት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም በዚህ መርሃ-ግብር ላይ ህዝቡ ያለ ስጋት ተሳትፎ እንዲያደርግ የጸጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።
የጸጥታ ኃይሉ የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ እና የበዓሉን ሰላማዊ ሁኔታ የማረጋገጥ ስራውን በላቀ ዝግጅት የሚያከናውን ይሆናል።
ስለሆነም መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበዓሉን ሰላማዊነት እንዲያስጠብቁም ጥሪ ቀርቧል።

