የሀገር ኩራት፣ የወገን መከታ፣ የጠላት ማርከሻ፣ የህዝብ ጋሻ!!

የሀገር ኩራት፣ የወገን መከታ፣ የጠላት ማርከሻ፣ የህዝብ ጋሻ!!

ከሀገር ፍቅር ከመነጨ ስሜት፣ ከወገን ሰላም መሻት ከተቀዳ ወኔ ከችግር ፊት እንደ ተራራ፣ ከህዝብ ፊት እንደ ጋሻ የቆመ ሰራዊት! የክልሉ የደጀን ኃይል።

ጀግንነት በአፍ በሚነገር ትረካ ሳይሆን በተግባር በሚገለፅ በክቡር ዋጋ ይተመናል። ለሀገር ክብር፣ ለወገን ሰላም በሚሰጥ ታማኝ አገልግሎት ይገለፃል።

በየትኛውም የግዳጅ ቀጠና የተሰጠውን ኃላፊነት ከገባው ቃለ-መሀላ ጋር አጣጥሞ መፈፀም ደግሞ የዚህ ጀግና ወታደር ዋነኛ መገለጫ ነው። ለህዝብ ሲል ምቾቱን፣ ለሀገር ሲል ህይወቱን በመገበር በወርቃማ ብዕር ወርቃማ የልብ ብራና ላይ ወርቃማ ታሪክን ይከትባል።

ሀገራችን በየዘመኑ ከሚገጥሟት ውስጣዊ እና ውጫዊ የፀጥታ ችግሮች የተፈጠሩ እና በትውልድ ቅብብሎሽ የፀናች ሀገርን የሚያስቀጥሉ፣ በፈተናዎች ፀንተው እና በችግሮች ተፈትነው ያለፉ አያሌ ጀግኖች ዛሬም ድረስ ይገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በብዙ ዘርፎች ማህበረሰቡን ፋታ የለሽ መከራዎችን እንዲያስተናግድ አድርገውታል። ይሁን እንጂ ይህን የህዝብ መከራ ለመቀልበስ የክልሉ የፀጥታ መዋቅ በርካታ መስዕዋትነት እየከፈለ ቆይቷል፤ እየከፈለም ይገኛል።

የክልሉን ሰላም የበለጠ ለማስፈንንና የፀረ-ሰላም ሀይሎችን የጥፋት ተልዕኮ በማክሸፍ ሀገርንና ህዝብን ለማገልገል ከተለያዩ የፀጥታ አካላትና መደቦች ተውጣጥተው ዋጋ እየከፈሉ ከሚገኙ የደጀን ሀይል የፀጥታ መዋቅርን ሚና ከሰራዊቱ አመራርና አባላት ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

በቆይታችን በምዕራብ ጎንደር ዞን ኮኪት ከተማ ዙሪያ ከሚገኘውና የተሰጠውን ህዝብና ሀገር የመጠበቅ ግዳጁን እየተወጣ የሚገኘውን የ2ኛ ሻለቃ 2ኛ ሻምበል የደጀን ሀይል የግዳጅ አፈፃፀምን ተመልክተናል።

የሻለቃው ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ሙላት ላቅያለው እንደሚሉት የደጀን ሀይሉ ከዞኑ ፖሊስ፣ ሰላም አስከባሪና ሚሊሻ አመራሮችና አባላት የተውጣጣ ሀይል መሆኑን በመጠቆም የተሰጠውን ህዝብን የመጠበቅ ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ኢንስፔክተር ሙላት ገለፃ የደጀን ሀይሉ በብዙ መንገድ የውጊያ ብቃትን፣ ወታደራዊ ስነ-ስርዓትን ጠንቅቆ የሚያውቅና በሀገር ፍቅር ስሜት የተገነባ ስነ-ልቦናን የተላበሰ በመሆኑ ግዳጁን በስኬት ለመወጣት ዝግጁ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የክልላችን ብሎም የሀገራችን ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የምንከፍለውን መስዕዋትነት አጠናክረን እናስቀጥላለን ሲሉም ምክትል አዛዡ ጠቁመዋል።

የሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው ለሀገር ሰላምና ለህዝባችን ደህንነት ስንል ቤት ንብረቴ ሳንል፣ ቤተሰብ ሳያሳስበን፣ ጫካው መኖሪያዬ ምሽጉ መጠለያዬ ብለን ተግባራችን በቆራጥነት እየተወጣን ነው ብለዋል።

አባላቱ እንደሚሉት ላኪ እና ተላላኪ ፀረ-ሰላም ሀይሎች የሀገራችንን ክብርና የህዝባችንን ሰላም ለማወክ እያደረጉት ያለውን ከንቱ ምኞት ለማክሸፍ ቁርጠኛ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top