የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አመራሮችና አባላት ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አመራሮችና አባላት ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ የትምህርት ዘመን መጀመርን አስመልክቶ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ ለማጠናከር፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አመራሮች፣ የወረዳ ፖሊስ አዛዦች እና አባላት በራሳቸው ፈቃድ ገንዘብ በማዋጣት የደብተር እና እስክሪፕቶ ቁሳቁስ ድጋፍ አከናውነዋል።

ድጋፉ ትናንት በተከናወነው ዓመታዊ የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ላይ የተሰበሰበ ሲሆን፣ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አመራሮች፣ የወረዳ ፖሊስ አዛዦችና አባላት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባላቸው ቁርጠኝነት የተከናወነ የበጎ አድራጎት ተግባር ነው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ተሾመ ብዙ እንደገለጹት፣ የፖሊስ ሰራዊቱ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ዋና ተግባሩ ቢሆንም ለአቅመ ደካማ ወገኖችና ለወደፊት ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች አጋርነት ማሳየት የዘወትር ባህሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዛዡ አክለውም ድጋፉ ተማሪዎች ያለምንም የስነ-ልቦና እና የቁሳቁስ ጫና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማስቻል የተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የተዘጋጀውን የትምህርት ቁሳቁስ ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ከኮማንደር ተሾመ ብዙ እጅ የተረከቡት የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ የስጋት ደሴ፣ ለተደረገው መልካም እና አርአያነት ያለው ተግባር የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ የስጋት ደሴ እንደተናገሩት፣ የፖሊስ መምሪያው አመራሮችና አባላት ያደረጉት ይህ በጎ አድራጎት ለሌሎች ተቋማት ትልቅ አርአያ የሚሆንና የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ የሚያጎለብት ነው ብለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top