ወንጀልን አምርሮ የሚጠላ ማህበረሰብ የተፈጠረባት፤ የአብሮነትና የሰላም ማሳያ፣ የነጭ ወርቅ ምድር ውብ ከተማ!
የምዕራብ ጎንደር ዞን መቀመጫ የሆነችው ገንዳውሃ ከተማ ሰላሟን አጠናክራ በማስቀጠልና ልማቷን በማሳለጥ ላይ ትገኛለች።
አሁን ላለችበት አንፃራዊ ሰላም የከተማዋ ማህበረሰብ፣ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት በማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል አሰራር ላይ ትኩረት ያደረገ የጋራ ጥረት መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች እና የፖሊስ አካላት ይመሰክራሉ።
የገንዳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ፅህፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር ኃይሌ ብርሃኑ እንደሚሉት በከተማዋ የሚፈጠሩ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን በመከላከል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከሚሊሻ፣ ሰላም አስከባሪ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም የማስጠበቅ ስራ የዕለት ከዕለት ተግባራቸው መሆኑንም ነው ኀላፊው የጠቆሙት።
እንደ ኢንስፔክተር ሃይሌ ገለፃ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት በተደረገ የወንጀል መከላከል ስራ የእገታ፣ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውው፣ የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።
ባለፈው በጀት ዓመት በወንጀል ምርመራ፣ በትራፊክ ቁጥጥር ስራና በህግ ማስከበር ተግባር የከተማዋ ፖሊስ ከፍተኛ ስራ መስራቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኀላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ባበይ ጨቅሉ እንደተናገሩት የከተማዋን ማህበረሰብ ተሳታፊ እና ባለቤት ያደረገ የወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማህበረሰቡ ለፖሊስ መረጃ ከመስጠትና ተባባሪ ከመሆን ባለፈ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ወንጀልን አምርሮ የሚጠላ ሆኗል ነው ያሉት ክፍል ኃላፊው።
በበጀት ዓመቱም በርካታ ህገወጥ ተተኳሾች፣ መሳሪያዎች እና የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውንም ረዳት ኢንስፔክተር ባበይ ጨቅሉ ጠቁመዋል።
አቶ ነጋ ሀይሌ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ሰላም በጋራ ጥረት የሚረጋገጥ የጋራ ሀብት በመሆኑ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን እና የተለያዩ አደረጃጀቶን በማዋቀር የከተማችንን ሰላም እየጠበቅን እንገኛለን ብለዋል።
በምሽት አካባቢያቸውን ሲጠብቁ ከነበሩት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ወይዘሮ ዘዋል ባዬ እና ወጣት ሲሳይ ጌታነህ እንደተናገሩት ከራስ ተነሳሽነት በመነጨ እና በከተማዋ ፖሊስ አደራጅነት እና አስተባባሪነት የወንጀል መከላከል ስራን እየሰራን ነው ብለዋል።
ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በጋራ በተሰሩ የሰፈር ጥበቃ፣ የወንጀል መከላከል ስራም ከዚህ በፊት ይከሰቱ የነበሩ የእገታ፣ የዝርፊያ፣ የንጥቂያና የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ወንጀሎች መቀነሳቸውን በመጠቆም ተግባሩን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም አመላክተዋል።







