የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት አስመረቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመሰረታዊ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን የአድማ መከላከል ፖሊስ ሰልጣኞች በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ሃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሸነር አብዮት ሽፈራው፣ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኮማንደር ይሰማ ተናኜ፣ የኢንስቲትዩቱ የሎጀስቲክስና የሰው ሃብት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሻምበል ዘመነን ጨምሮ ሌሎች የፖሊስ መኮንኖችና አባላት ተገኝተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥልጠና ሪፖርት ያቀረቡት ኮማንደር ይሰማ ተናኜ፤ ተመራቂዎች በቀጣይ ክልላዊ ተልዕኮዎች ላይ በብቃት መሳተፍ የሚያስችላቸውን አስፈላጊ ወታደራዊ እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ መደረጉን ገልጸዋል።
ኮማንደር ይሰማ አክለውም አባላቱ የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግሥት አደራ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸው የአመለካከትና የተግባር አንድነት መገንባቱን አስረድተዋል።
በምረቃው ላይ በመገኘት የሥራ መመሪያ የሰጡት ረዳት ኮሚሸነር አብዮት ሽፈራው በበኩላቸው፤ ተመራቂ አባላት በክልሉ ሕግን የማስከበር ሂደት ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን አሳስበዋል።
በሥልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀትና ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመጠቀም ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም አክለው ገልጸዋል።
ረዳት ኮሚሸነሩ አክለውም አባላቱ የተቀላቀሉት ተቋም የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ለመወጣት አቅሙን በቴክኖሎጂ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይልና በሎጀስቲክስ አቅርቦት እያደራጀ የሚገኝ፣ እንዲሁም ለሠራዊቱ ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ትጋት እየሠራ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
በመሆኑም በርካታ ጀግና የሕዝብ ልጆችን ያፈራና በፈጣን የለውጥ ጉዞ ላይ በሚገኝ ተቋም ውስጥ መቀላቀላችሁ የኩራትና የጀግንነት ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ረዳት ኮሚሸነር አብዮት ሽፈራው ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ፣ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ከሚገኙ የአድማ መከላከልና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የተጣለባቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት በውጤታማነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ተመራቂ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት በበኩላቸው በቆይታቸው የወሰዱት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከፍተኛ መነሳሳትና ዝግጁነት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።





