ከ64 ዓመታት በኋላ የተደረገው የሕግ ማሻሻያ እና በወንጀል ምርመራ ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅዕኖ!
አዲሱን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ በአግባቡ ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ በፌደራል ፍትሕ ሚኒስቴር እና በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ትብብር ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
ነባሩ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ64 ዓመታት በላይ የተቆጠረ በመሆኑ፣ አሁን ከደረስንበት የአስተሳሰብ፣ የሕግ እና የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የማይመጥን በመሆኑ በምትኩ ዘመናዊና ጊዜውን የዋጀ አዲስ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ (አዋጅ ቁጥር 1410/2018) መጽደቁ ተገልጿል።
ሕጉን በተመለከተ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሰራው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት አዲሱ ሕግ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ከሀገሪቱ መልካም እሴቶች እና ባህሎች ጋር አዋህዶ የያዘ ነው። በተጨማሪም ከፖሊስ የምርመራ ደረጃ ጀምሮ እስከ ማረሚያ ቤት እስከ ማረም እና ማነጽ ድረስ ያሉ አሠራሮችን ፍትሐዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚመራ ነው ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው አክለውም ቀደም ሲል በስህተት ተፈርዶበት እስር ቤት የገባን ሰው ስህተቱን አርሞ ለመልቀቅ የሚያስችል የሕግ ሥርዓት ያልነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ሕግ ግን በስህተት የተፈረደበት ሰው ፍርዱ እንደገና የሚታይበትና ለደረሰበት በደልና አደጋ ካሳ የሚከፈልበትን አሠራር በግልጽ አስቀምጧል።
የሴቶች፣ የሕፃናት እና የተጎጂዎችን መብት ያከበረ የዋስትና አሠራር የተዘረጋ ሲሆን፣ አቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም ማስረጃ ሲያጣ ብቻ ክስ ይዘጋ ከነበረበት አሠራር ወጥቶ፣ አሁን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስን ማቋረጥ ወይም ማስቀጠል የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በማብራሪያቸው።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሕጎች ተሰባጥሮ የነበረውን የማስረጃ ሕግ በጥቅል አደራጅቶ የትኞቹ ማስረጃዎች ተቀባይነት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለይቷል ያሉት አቶ ወንዳቸው፤ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን እና አማራጭ የሙግት መፍትሔዎችንም አካቷል ሲሉ አክለዋል።
በወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የተፈረደባቸው አካላትን ከሌሎች ሀገራት አሳልፎ ከመስጠት እና ከመቀበል ጋር ተያይዞ በሕግ የተደገፈ ግልጽ ሥርዓትም መዘርጋቱም ተመላክቷል።
በሥልጠናው ላይ የተሳተፉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንለይ መኮንን በሰጡት አስተያየት አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ በፖሊስ የሕግ ማስከበር እና የምርመራ ሥራ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮማንደር አንለይ አክለውም መርማሪ ፖሊሶች የሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የተጠረጠሩ ሰዎችን መብት የመጠበቅ እና የጊዜ ቀጠሮዎችን በሕጉ በተቀመጠው አጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ፍትሕን የማፋጠን ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት ይህ ሥልጠና ከፍተኛ እውቀት እንደሚያስጨብጣቸው ገልጸዋል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እንዳመላከተው የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማና ወጥ ይሆን ዘንድ የፍትህ ተቋማት ሕጉን አውቀውና ተገንዝበው እንዲተገብሩት ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ሥልጠና በዞንና በክልል ደረጃ ሳይወሰን እስከ ወረዳ ድረስ ተከታታይነት ባለው መልኩ የሚሰጥ ይሆናል።







