“የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት ለማስከበር በተቋማት መካከል የሚደረግ የተቀናጀ አሰራር እና ጠንካራ ትብብር ወሳኝ ነው!!”
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የተመራ ከፍተኛ የአመራር ልዑካን ቡድን በሁለተኛ ቀን የባህር ዳር ቆይታው በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ እና ለልዑካን ቡድኑ የክብር ማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያዎች ግንኙነትና ትብብር የህዝብን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ የልማት ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
“የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት ለማስከበር በተቋማት መካከል የሚደረግ የተቀናጀ አሰራር እና ጠንካራ ትብብር ወሳኝ ነው!!” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ልምድ እና መረጃ በመለዋወጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ይህን ወንድማማችነታዊና ሙያዊ ትስስር አጠናክሮ ማስቀጠል የህዝብን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት በሁለቱ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያዎች መካከል ያለውን የሙያና የቴክኖሎጂ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክርና ለወደፊት የጋራ ህግ ማስከበር ስራዎች ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተመልክቷል።
















