ሰው በማገት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ፣ ሰው በማገት ወንጀል የተጠረጠሩ 8 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ጉዳዩ የተከሰተው ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም ሲሆን፣ ቢኒያም ጉልላት የተባለ ወጣት በአንዲት ሴት ተታልሎ ወደ መዝናኛ ቦታ ከተወሰደ በኋላ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግቶ ወደ ጫካ ተወስዷል። አጋቾቹ ቤተሰቡን በስልክ በማስፈራራት ገንዘብ ጠይቀው፣ ቤተሰቡ 3 ሚሊዮን ብር በመክፈላቸው ታጋቹ ተለቋል።
የጣይቱ እና የአጼ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተማ ፖሊሶች በጋራ ባደረጉት ምርመራና ክትትል፣ እንዲሁም በማህበረሰብ ጥቆማ ተጠርጣሪዎቹ ተይዘዋል ሲሉ የፖሊስ መምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ገብረመስቀል ቦጋለ ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ሁለት ሽጉጦች (ከ10 ጥይቶች ጋር)፣ አንድ ቦንብ፣ 400,000 ብር ጥሬ ገንዘብ፣ 7 ሞባይል ስልኮች፣ 2 ባጃጆች እና የተለያዩ የባንክ ደብተሮች የተያዙ ሲሆን ምርመራው በሒደት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ወጣቶች ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር በጥንቃቄ እንዲነጋገሩ እንዲሁም ማህበረሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ህገወጦችን በመጠቆም የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።




