“የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ያለው ሰፊ የሪፎርም እና የለውጥ ሂደት የፖሊስ ሰራዊቱን የማስፈጸም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረና ወቅታዊ የህግ ማስከበር ፍላጎቶችን በሚገባ ለመመለስ ያስቻለ ትልቅ ምዕራፍ ነው!” ሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የተመራ ከፍተኛ የአመራር ልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት እና የሁለትዮሽ ውይይት ባህር ዳር ከተማ ገብቷል።
ልዑካን ቡድኑ ባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ እና በዋና ጠቅላይ መምሪያው የማኔጅመንት አባላት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
የልዑካን ቡድኑ በባህር ዳር ቆይታው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ያከናወናቸውን የሪፎርም እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን ከክልሉ ፖሊስ አመራሮች ጋርም ሰፊ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል።
ልዑካኑ በጉብኝታቸው ወቅት በዋና ጠቅላይ መምሪያው እና በቴክኖሎጂ ክፍሎች የተከናወኑ ስኬታማ የለውጥ ስራዎችን፣ በሪፎርሙ የተፈጠሩ ምቹ የሥራ አካባቢዎችን እንዲሁም የዳታ ቤዝ እና የንብረት አያያዝ ሥርዓቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከሪፎርሙ በፊት ይባክን የነበረውን የባለሙያ ጉልበት፣ ጊዜ እና ሀብት ያስቀረው ዘመናዊው የዲጂታል ዳታ አያያዝ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሚሆን መሆኑን አመራሮቹ ገልጸዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አመራሮችም በሰጡት ዝርዝር አስተያየት ተቋሙ አሰራሩን ቀልጣፋ ለማድረግ እና አገልግሎቱን ወደ ህብረተሰቡ ለማቅረብ በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ እና በሰው ኃይል አስተዳደር የዘረጋው መዋቅራዊ አደረጃጀት በእጅጉ የተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ የታየው የሥራ አካባቢ ምቹነት፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት እና የቴክኖሎጂ ፍላጎት ተቋማዊ አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን በጎ ተሞክሮ ወደ መዲናዋ ፖሊስ አሰራር ለማስገባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው ፖሊስ እንደ ተቋም ራሱን በዘመናዊ አሰራር፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በተደራጀ መዋቅር ሲገነባ የህዝብን ደህንነት የማረጋገጥ እና ወንጀልን የመከላከል አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎለብታል፤ በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች በተለይም የፖሊስ አገልግሎትን ተደራሽ እና ፈጣን ለማድረግ የተሄደበት ርቀት የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና ፈጣን እንዲሁም ፍትሃዊ የምርመራ ውጤት ለማስገኘት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉም ኮሚሽነር እርዚቅ አክለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ውጤታማነት አስጠብቆ ለመቀጠል የሚያደርገውን ጥረት አደንቃለሁ። ይህ የሪፎርም ሂደት የውስጥ ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ክልሎች ፖሊስ ተቋማት ጋር የሚደረገውን የጋራ ወንጀል የመከላከል ስራ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ በጉብኝቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት “የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ያለው ሰፊ የሪፎርም እና የለውጥ ሂደት የፖሊስ ሰራዊቱን የማስፈጸም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረና ወቅታዊ የህግ ማስከበር ፍላጎቶችን በሚገባ ለመመለስ ያስቻለ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።
እንደ ሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ ገለጻ ይህ የልምድ ልውውጥ ተቋሙ ወዴት እየሄደ እንዳለና ሥራው በምን አይነት ሁኔታ እየተመራ እንዳለ በሁሉም አመራር ዘንድ ወጥ ግንዛቤ እንዲፈጥር የሚያስችል ነው።
ሁለቱም የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያዎች ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎትን ለዜጎች ለማድረስ ለሚያደርጉት ጥረት፣ ለሙያዊ እድገት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ግብዓት የሚገኝበት ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመስራት ህግና ስርዓትን ለማስከበርና የህዝቡን ደህንነት በተሻለ ደረጃ ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ሌተናል ጀኔራል አስራት ደኔሮ አክለው አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የፖሊስ ተቋም አገልግሎትን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
የሁለቱ ተቋማት የጋራ ትብብርና የልምድ ልውውጥ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የወንጀል መከላከል አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉም አክለዋል።
የወንጀል ቅርፅና ስልት እየተቀየረ በመጣበት በዚህ ወቅት በቴክኖሎጂ እና በመረጃ ልውውጥ ላይ የተመሰረተ የጋራ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን በማለት ቀጣይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በመገኘት ተሞክሮ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም የሁለቱን ተቋማት አጋርነትና ወንድማማችነት የበለጠ ለማጠናከር ሲባል በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በኩል ለልዑካን ቡድኑ የማስታወሻ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማስታወሻ ስጦታ አበርክቷል።





















