የሠላም አማራጭን የተቀበሉ ህገ-ወጥ ታጣቂዎች እጅ ሰጡ።
በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ በምድማርና አባማር አከባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን አባላት ለ10ኛ ዕዝ መብረቅ ክፍለጦር እጅ መሥጠታቸው ተገለጸ።
ከአካባቢው ሽማግሌዎችና የአመራር አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በአካባቢው የነበሩ ህገ-ወጥ ታጣቂዎች እንዲገቡና የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ የማድረግ ሥራ ሠርተናል ሲሉ የመብረቅ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ስንታየሁ ሰዒድ ተናግረዋል።
እጅ የሰጡ ታጣቂዎች በበኩላቸው የራሳችንን ሰላም በማጣት ለአካባቢው ሰላም መታወክ ምክንያት ሆነን ቆይተናል ከዚህም የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን ተረድተን ሠላምን በመምረጥ እጅ ሰጥተናል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን ተሰማርቶ ግዳጁን እየተወጣ የሚገኘው መተማ ክፍለጦር በአንጎት ወረዳ ተረፌ አካባቢ በህገ-ወጥ ታጣቂ ሀይል ላይ ርምጃ በመውሰድ ኪሳራ ማድረሱ ተጠቁሟል ።
የክፍለጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ጎሹ ዘገየ እንደገለጹት ክፍለጦሩ በወሰደው እርምጃ በርካቶችን ሙትና ቁስለኛ ማድረጉን ጠቁመው መሳሪያና ተተኳሽ ቀብሮት ከሸሸው ፀረ ተሽከርካሪ TM 57 ፈንጅ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።



