የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄደ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮች፣ አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች በተገኙበት የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅና ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና ስታፍ ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መልሰው ሞላ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ዋና ዋና ግቦችን ያቀረቡ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የተቋሙን የመፈጸም አቅም ማሳደግ እና የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚታየውን የፖሊስ አመራርና ባለሙያ እጥረት ለመፍታት የሰው ኃይል ማሟላት፣ የፖሊስ ሠራዊቱን፣ መምህራንና አሰልጣኞችን አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ችግር ፈች ጥናቶችና ምርምሮችን ማካሄድ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ሽግግርን በማሻሻል አሰራርን ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረግ የሚሉ በዕቅዱ የተጠቀሱ ናቸው።
የተቋማዊ ሪፎርም ስራዎችን ማጠናከር፣ የህግ ማቀፎች ክፍተትን ለይቶ ማሻሻል፣ የበጀትና ንብረት አያያዝን እንዲሁም የውስጥ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አሰራርን ማዘመን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
እንደ ኮማንደር መልሰው ገለጻ የፖሊስ አባላትን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መመሪያ የተያዙ ግቦችን ማሳካት የሚቻለው በአመራሩና በሙሉ ሠራተኛው የተቀናጀ ጥረት መሆኑን አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ተቋሙን ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ገጽታውን ለመገንባት ከሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር ያለው ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የፖሊስን ታሪክ የሚያጎላ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሙዚየም ማደራጀትና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮችና አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን በዕለቱም በአመራሮች መካከል የታቀዱ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የዕቅድ ስምምነት ፊርማ እና የዕቅድ ርክክብ ስነ-ስርዓት ተፈጽሟል።






