ስለ-ወገን እየኖረ፣ ስለ ሀገር የሚሞት፤ የታላቅ ህዝብ ሰላም ጠባቂ ጋሻ! የአማራ ክልል አድማ መከላከል ፖሊስ።
የጀግንነት መነሻ፣ የኃያልነት መዳራሻ፣ የመከራ ቀን ማለፊያ፣ የታሪክ መጻፊያ ብዕር፣ የሁልጊዜ መኩሪያ፣ የጨለማ ቀን መውጫ መንገድ፣ የታላቅ ሕዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ፤ ከሰንደቅ በፊት ይዋደቃል። መነሻው የህዝብ ፍቅር፣ መዳረሻው የሀገር ክብር ነው።
የአማራ ክልል አድማ መከላከል ፖሊስ ስሙ በአሸዋ ላይ ተጽፎ የሚጠፋ ሳይሆን፣ በትውልድ ልብ ውስጥ በክብር የሚቀረጽ የጀግንነት ምልክት ነው። የሀገር ሉዓላዊነት እንደ ቅዱስ አደራ በእጁ ይዞ፣ የህዝብን ሰላም እንደ የራሱ ክብር ቆጥሮ የሚቆም የኢትዮጵያ ጽኑ አምባ ነው። የሌሎች እረፍት እንዲጸና የራሱን እንቅልፍ የሚሰጥ፣ የነገ ተስፋ እንዳይደበዝዝ ዛሬን በጽናት የሚሻገር ጀግና ነው።
የዚህ ጀግንነት ምንጭ ግን ከመሣሪያ ጉልበት በላይ በውስጡ የሚነደው የሀገር ፍቅር ነው። የራሱን ምቾት በህዝብ እረፍት የሚለውጥ፣ የግል ምኞቱን በሀገር ዓላማ የሚተካ፣ በአደጋ ውስጥ እንኳን ተስፋን የማይለቅ የተቀደሰ ተልዕኮ ተሸካሚ ነው። ዩኒፎርሙ በሰውነቱ ላይ የተለበሰ ጨርቅ ብቻ አይደለም፤ የሀገር አደራ፣ የህዝብ ተስፋን እና የታሪክ ክብርን በትከሻው ላይ የተሰጠው ማህተም ነው።
የአማራ ክልል አድማ መከላከል ፖሊስ ጀግና ወታደር የሀገር ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የክብር ታሪክ የሚያስቀጥል ሕያው ካስማ ነው። የሚያልፈው ዘመን አካሉን ቢያደክምም የሀገር ፍቅሩን ቅንጣት ታክል አያጎድለውም፤ የሚገጥመው ፈተና ቢበዛም የተሰጠውን አደራ ከልቡ አያወጣውም።
ከዚህ የህዝብ ጋሻ የሰላም ሰራዊት ሻለቃዎች ውስጥ በጎንደር ዙሪያ መገጭ አካባቢ የግዳጅ ቀጠናውን በማድረግ ህግ እያስከበረ የሚገኘው የዘጠነኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስን የግዳጅ አፈፃፀም ከሻለቃው አመራሮችና አባላት ጋር ከቦታው ተገኝተን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
የሻለቃው አዛዥ ምክትል ኮማንደር አይቀርም መላኩ እንደተናገሩት የክልሉን ሰላም እያደፈረሱ የሚገኙ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን በማፅዳት የህዝባችንን ሰላም ለማረጋገጥ የምንከፍለው መስዕዋትነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮማንደር አይቀርም መላኩ ገለፃ ሻለቃው ከሀገር መከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራ በመጠቆም ሰራዊቱ በስነልቦና፣ በሎጂስቲክ እና በወታደራዊ ዝግጁነት የታነፀ መሆኑን በመጠቆም በበርካታ የውጊያ ቀጠናዎች ላይ ስኬታማ ግዳጆችን ፈፅሟል ሲሉ ተናግረዋል።
የሻለቃው የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አዳነ ያይኔ በበኩላቸው የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ሰራዊቱ እያደረገ ያለው የህግ ማስከበር ስራ ውጤት በማስመዝገቡ ማህበረሰባችን እፎይታ እያገኘ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
የሻለቃዋ አባላትም እንደሚሉት የምናደርገው ሁለንተናዊ ትግልና የምንከፍለው መስዕዋትነት ለአማራ ህዝብ ሰላምና ለክልሉ ብሎም ለሀገራችን ክብር በመሆኑ ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት።
ልፋታችን ለሰላም፤ መስዕዋትነታችን ለህዝባችን ነው! የሚሉት አባላቱ የክልላችን ሰላም እስኪረጋገጥና የህዝባችን ነፃነት እስኪፀና ድረስ ትጋላችን ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።








