የኮሚሽነር ጀኔራል ተጠሪ ዋና መምሪያዎች እና መምሪያዎች የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሄደ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚሽነር ጀኔራል ተጠሪ ዋና መምሪያዎች እና መምሪያዎች የተሳተፉበት የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል።
የዕቅድ ትውውቅ ሰነዱን ያቀረቡት ኮማንደር ነጋ ድንበሩ በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚደረግባቸውን ዋና ዋና ግቦችና ተቋማዊ አቅጣጫዎች አብራርተዋል።
የሕግ የበላይነትንና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የላቀ ሙያዊ አገልግሎት መስጠት፣ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን ማጠናከር የበጀት ዓመቱ ዋነኛ የትኩረት መስኮች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
ኮማንደር ነጋ አክለውም የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር ተቋማዊ አሰራርን ማሳደግ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መለየት፣ ማበልጸግና ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማሳደግ፣ የስራ ክፍሎችን ተልዕኮ የሚያቀናጅ ስርዓት መቅረጽ፣ ውጤታማ የበጀት ፍላጎት ዕቅድ ማዘጋጀትና በቁጠባ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አንስተዋል።
የተቋሙን ህጋዊ ጥቅም ማስከበር፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የተቋሙን ገጽታ መገንባትና የህብረተሰቡን አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባም በበጀት አመቱ በትኩረት ከሚተገበሩ አንኳር ስራዎች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።
በቅድመ ወንጀል መከላከል ላይ የተመሰረተ የመረጃ አቅምን ማሳደግ እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎችና ከፍትህ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባም ነው ኮማንደር ነጋ ድንበሩ ያብራሩት።
በመድረኩ የተሳተፉ አመራርና አባላት በበኩላቸው የታቀዱትን ግቦች ለማሳካት ቅንጅታዊ አሠራርና የቁርጠኝነት አስፈላጊነትን አንስተዋል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም በበጀት ዓመቱ የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት አመራሩና አባሉ በተግባርና በአመለካከት አንድነት በመቆም፣ የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰሩና የክልሉን ሰላምና የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
መድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች በኩል ተጨማሪ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የተጣለብንን ተቋማዊ ኃላፊነትና የታቀዱትን ግቦች ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነትና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኮሚሽነር ጀኔራል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው በዕቅድ ትውውቅ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር የታቀዱ ግቦች ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲቀየሩ የአመራሩና የመላው አባላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ገለጻ የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎች ለክልሉ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ካላቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንጻር በትኩረት እንዲፈጸሙ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በማጠናከር የተቋሙን ገጽታ ማሻሻል፣ በቅድመ ወንጀል መከላከል ላይ የተመሠረተ የመረጃና ክትትል አቅምን ማሳደግ እና የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች መካከል የታቀዱትን ስራዎች በውጤታማነት ለማስፈጸም የሚያስችል የዕቅድ ስምምነት ፊርማ እና የርክክብ ስነ-ስርዓት በመፈጸም የመድረኩ ፍጻሜ ሆኗል።








