የከተማዋን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥ ከህዝብ ጋር በጋራ የሚተጋ የሰላም ሀይል
የጎንደር ከተማ አስተዳደርን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል በማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ተግባር ላይ የተመረኮዘ አሰራርን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ።
የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል አሰራር ሲሆን ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ሳንካ ምክንያት በአብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢዎች ውስጥ በመቋረጡ አተገባበሩ በብዙ መልኩ ተቆራርጦ ቆይቷል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አሰራሩን ዳግም እንዲያንሰራራ በማድረግና ውጤታማነቱን በተግባር በማረጋገጥ ለውጥ የታየበት ስራን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
የጎንደር ከተማን ሰላም የበለጠ ለማፅናት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ እና የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር ስማቸው ፈንታ እንደተናገሩት የከተማዋን አሁናዊ ሰላም የበለጠ ለማስቀጠል ማህበሰሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ጽንሰ-ሀሳብ ወንጀልና ወንጀለኛን ለመቆጣጠር አይነተኛ ሚና አለው የሚሉት ኃላፊው በከተማዋ ይፈፀሙ የነበሩ የእገታ፣ የዝርፊያ፣ የግድያ እና ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ኢንስፔክተር ስማቸው ገለፃ የከተማዋን ነዋሪዎች ስጋት የሚቀንሱ እና የልማት ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ የተጠናከረ የወንጀል መከላከልና የሰላም ማስፈን ስራ በቀንና በሌሊት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አብራርተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የአንደኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር መንገሻ አውደው በበኩላቸው ሰላም በፀጥታ ሀይሉ ፍላጎትና ጥረት ብቻ የማይመጣ ከመሆኑም ባሻገር ያለ ማህበረሰቡ ተሳትፎ ውጤት አልባ ድካም በመሆኑ ከተማዋ ፖሊስ እና ማህበረሰብ በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አቶ ፍትጉ አበረ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የጋራ ሰላማችንን የበለጠ ለማፅናት ከወጣቶች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች የተውጣጡ አካላት ከፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን በተለያዩ አደረጃጀቶች እና አወቃቀሮች በመደራጀት የወንጀል መከላከል ስራን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላው በምሽት አካባቢያቸውን ሲጠብቁ ካገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ስመኘው ሙሀባው እንዳሉት ሰላም በጋራ ጥረት የሚመጣ፣ ለጋራ አብሮነት መሰረት የሆነ የጋራ ሀብት በመሆኑ ከከተማዋ የፖሊስና ልሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ወንጀልንና ወንጀለኛን የመቆጣጠር ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።







