የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የሬዲዮ መገናኛ ሙያተኞችን አሰመረቀ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የስራ ቅልጥፍናንና የመረጃ ልውውጥን ለማዘመን ሲሰጥ የቆየውን የመገናኛ ሬዲዮ ስልጠና ያጠናቀቁ ሙያተኞችን አሰመረቀ።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንደገለጹት ፈጣንና አስተማማኝ የመረጃ ልውውጥ ለወንጀል መከላከል ስራ ስኬት መሰረት መሆኑን አስታውቀዋል።
ተመራቂዎች የወሰዱትን ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እውቀት መሬት ላይ በማውረድ ህብረተሰቡን ከወንጀልና ከስጋት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን የጎላ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፖሊስ ግልጽ፣ ፈጣንና ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ የመረጃ ስርዓት እንዲኖረው የሬዲዮ መገናኛ ሙያተኞች ሀላፊነት ከፍተኛ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሰው ሀብት ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው፣ የፖሊስ ሰራዊቱን ሙያዊ ብቃትና ዝግጁነት ለማሳደግ የሚረዱ ይሄን መሰል ልዩ ልዩ የሙያ ስልጠናዎች አስቀድሞ በተያዘው ተቋማዊ እቅድ መሰረት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሬዲዮ መገናኛ ዋና ክፍል ተወካይ ምክትል ኮማንደር ዳንኤል በሀብላ በበኩላቸው ስልጠናው በዘመናዊ የመገናኛ መሳሪያዎች አጠቃቀም፣ በቴክኒክ ጥገና፣ በሚስጥር አያያዝ እና በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ልውውጥ ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።
ተመራቂዎቹ በንድፈ-ሀሳብና በተግባር ያገኟቸውን ክህሎቶች በመጠቀም የተጣለባቸውን የሙያ ሀላፊነት በተሻለ ብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ምክትል ኮማንደር ዳንኤል አረጋግጠዋል።
በምረቃው ማጠቃለያ ላይ ለሰልጣኞች ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ተመራቂዎችም ያገኟቸውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የህዝብንና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።









