በበየዳ ወረዳ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ገቡ
በሰሜን ጎንደር ዞን በበየዳ ወረዳ በተከዜ፣ በበስቂያ፣ በጠዘን፣ በሰገነት እና በአበርገሌ አካባቢዎች ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ኃይሎች፣ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ገብተዋል።
የተከዜ ብርጌድ አዛዥ ሻለቃ እንዳልክ ፍቃዱ ከ10 አባሎቻቸው ጋር በመሆን፡
* 1 ብሬን
* 4 ክላሽንኮቭ
* 1 እስኬስ
* 1 ምንሽርና 1 አብራራው የተሰኙ የጦር መሣሪያዎችን በማስረከብ ነው በዛሬው ዕለት ወደ በየዳ ወረዳ የገቡት።
በአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የበየዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸጋው ብርሃን፣ ጥሪውን ተቀብለው በሰላም በመመለሳቸው ምስጋና አቅርበዋል።
“ከግጭት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን በመረዳት ወደ ሰላም መመለሳችሁ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤ ከዚህ በኋላም ለአካባቢው ሰላም ዘብ ልትቆሙ ይገባል” ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የ70ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ተስፋሁን ቤኬ በበኩላቸው፣ እርስ በእርስ መጋጨት ሰላምንና ልማትን ወደኋላ ከማስቀረት ውጭ ምንም ጥቅም እንደሌለው ጠቁመዋል።
አዛዡ ሌሎች በጫካ የሚገኙ ሕገ-ወጥ የታጠቁ ኃይሎችም ይህንን የሰላም አማራጭ በመከተል ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከተቀላቀሉት መካከል የራስ አሞራው ውብነህ 3ኛ ኮር ሰሜን ብርቅዬ ክፍለጦር የተከዜ ብርጌድ አዛዥ ሻለቃ እንዳልክ ፍቃዱ ፣ የሰላም ጥሪውን በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ቀደም ሲል የነበራቸው አካሄድ የተሳሳተና የሕዝብን ሰላም የሚነሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ በልማት እና በሰላም ግንባታ ላይ በንቃት በመሳተፍ ሕዝባቸውን ለመካስ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።



