የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮችና መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና እየወሰዱ ነው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮችና መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና እየወሰዱ ነው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከተሰጠው ተቋማዊ ደረጃ ጋር የሚመጥን የትምህርት ጥራትና ህጋዊ የዕውቅና መስፈርት ለማሟላት የሚያስችለውን የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአመራሮቹና ለተቋሙ መምህራን መስጠት ጀምሯል።

ስልጠናው የተዘጋጀው ከአፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ጋር በመተባበር ሲሆን በዋናነት በከፍተኛ ትምህርት ምዝገባ፣ የፈቃድ አሰጣጥ ሂደቶች እና ተቋማዊ መስፈርቶች አፈጻጸም ዙሪያ ያተኮረ ነው።

የስልጠናውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ እንደገለጹት ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማደጉን ተከተሎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠይቁትን መስፈርት በሙሉ በማሟላት ከሌሎች ሀገራዊ የትምህርት ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት አለበት።

ምክትል ኮሚሽነር አበበ አክለውም ተቋማችን ከስም ለውጥ ባለፈ በተግባር እንደ ደረጃው ሆኖ ለመገኘት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል ብለዋል።

ይህ ስልጠና በቀጣይ ለምናዘጋጀው የፈቃድ ጥያቄ ሰነድ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ለመጨበጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ላደረገው ፈጣን ምላሽ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በቀጣይ በሚዘጋጁ ተቋማዊና ህጋዊ ሰነዶች ላይም የባለሙያዎች ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።

ከኢፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የመጡት አሰልጣኝ ባለሙያዎች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ያቀረባቸውን የህግና የደረጃ ጥያቄዎች ለማሟላት ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ተቋሙን በሙያዊ መስክ ለማገዝ ሙሉ ዝግጅት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ፤ የትምህርት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሰነዶችን የሚያዘጋጁ መምህራንና አመራሮች የስልጠናውን ጭብጥ በአግባቡ በመከታተል የተጣለባቸውን ተቋማዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለ2 ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ይህ ስልጠና የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን የትምህርት ጥራትና ህጋዊ ተቀባይነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top