“የህዝብ አመኔታና ትብብር ዋና መሳሪያ በመሆኑ ህብረተሰቡን በእኩልነትና በቅንነት ማገልገል ይገባል!” ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ከክልልና ከዞን የወንጀል ምርመራ አመራሮችና አባላት ጋር በበይነ-መረብ (ኦንላይን) የታገዘ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅና የውል ስምምነት ፊርማ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ አባላቱ በአስቸጋሪና ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቅ የወቅቱ የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ያልተቆጠበ መስዋዕትነት አድንቀዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው አክለውም የምርመራ ሀላፊዎችና አባላት በስራ ዘመኑ ሊመሩባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ቁልፍ አቅጣጫዎችን አስታውቀዋል።
አስቸጋሪ አካባቢዎች ላይ የሚካሄድ ምርመራ በልማዳዊ አሰራር ሳይሆን በፎረንሲክ፣ በላቦራቶሪና በሰው መረጃ (HUMINT) ተደግፎ በጠንካራ የህግ ማስረጃ ላይ ብቻ ሊመሰረት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ተቋሙ ከህገወጥ ታጣቂዎች የሚለየው ህግንና ስነ-ምግባርን በማከበሩ እንደሆነ ጠቅሰው የተጠርጣሪዎች አያያዝና ምርመራ ሙሉ በሙሉ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ያከበረ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የምርመራ ቡድኖችን ደህንነት መከታተል፣ የመረጃ ፍሰትን መጠበቅና የተጠርጣሪዎችን ዝውውር በጥንቃቄ መምራት የየክፍሉ ሀላፊዎች ቀዳሚ ሀላፊነት መሆኑ ተመላክቷል።
የህዝብ አመኔታና ትብብር ዋና መሳሪያ በመሆኑ ህብረተሰቡን በእኩልነትና በቅንነት ማገልገል እንደሚገባና ከሌሎች የፀጥታና የፍትህ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የምርመራ ስራ ጥራትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ዘመናዊ የዳታ አያያዝ ስርአትን መጠቀምና በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተጣለባቸውን ሀላፊነትና የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በላቀ ቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ በጠቅላይ መምሪያው ስር ባሉ ዋና መምሪያዎች እና ምክትል ዋና መምሪያዎች መካከል የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ርክክብና የውል ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓት ተፈጽሟል።








