“ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ደህንነት ሲባል መስዋዕትነት የሚከፈልበት ክቡር ሙያ ነው!” ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ከተቋሙ ከፍተኛ መኮንኖች እና ኮሚሽነሮች ጋር በክልሉ ነባራዊ የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ።
በውይይቱ ወቅት አዛዡ እንዳመለከቱት ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሰላም ሲባል መስዋዕትነት የሚከፈልበት የተከበረ ሙያ መሆኑን ገልጸው አመራሩና አባላቱ ለሙያው ተገቢውን ክብር በመስጠት በላቀ ሙያዊ ብቃት (ፕሮፌሽናሊዝም)መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በየደረጃው በሚገኝ የፖሊስ ሰራዊት ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረትና የሚከፍሉት ዋጋ ፍሬያማ መሆን እንዳለበት ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ አሳስበዋል።
ክልሉ ከገባበት የፀጥታ ቀውስ በፍጥነት እንዲወጣ ሁለንተናዊ የሆኑ መደበኛ እና ሕግ የማስከበር ሥራዎችን በብቃት፣ በትጋትና በስኬት ማጠናቀቅ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ለፖሊስ ሙያ ተገቢውን ክብር መስጠት ለፖሊስ መርሆዎች ሙሉ በሙሉ ተገዥ መሆንና የሙያ ሥነ-ምግባርን ማክበር እንደሚገባ ያስገነዘቡት ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ሕዝብን ያሳተፈ ዘመናዊ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ቀበሌዎችን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች በማጽዳት የሕዝቡን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥን በትኩረት ልንሰራባቸው ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
እንደ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ገለጻ ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራርና የቡድን ሥራ የበለጠ ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉ አብራርተዋል።






