“ፖሊስ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር፣ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎችን በጥራትና በብቃት የመወጣት ታላቅ ኃላፊነት አለበት!” ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ በዋና ጠቅላይ መምሪያው ሥር የሚገኙትን የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያዎችን እንዲሁም የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ቢሮዎች እና የእለት ተእለት የስራ እንቅስቃሴ በጥቅል በአካል በመገኘት ተዘዋውረው ጎበኙ።
በጉብኝታቸው ወቅት በየክፍሎቹ የተፈጠሩትን ምቹ እና ዘመናዊ አሰራሮች ያደነቁት ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ “ፖሊስ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር፣ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎችን በጥራትና በብቃት የመወጣት ታላቅ ኃላፊነት አለበት!” ሲሉ አሳስበዋል።
የተቋሙን አጠቃላይ የሪፎርም እንቅስቃሴ፣ የህዝብ ግንኙነት ሚና እና በቀጣይ የሚከናወኑ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን መሰረት ያደረጉ ዋና ዋና ነጥቦችን አዛዡ በጉብኝታቸው ጠቅሰዋል።
የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የተቋሙን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ የግዳጅ አፈጻጸምን፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና ተቋማዊ ዕቅዶችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ በኩል የጎላ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የተቋሙን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በማርች ባንድ እና በኪነት ቡድኑ በኩል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ የተሰራ ሲሆን፣ በቀጣይ በጀት ዓመትም አቅምን የሚያጎልብ የሙያ ስልጠና ይሰጣል ሲሉ አዛዡ አክለዋል።
በህዝብና በፖሊስ መካከል ያለውን የመረጃ ልውውጥና የተቀናጀ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ መረጃዎችን በጥራት ለህዝብ ማድረስ እና ህዝባዊ አመኔታን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለኮሙኒኬሽን ዘርፍና ለሌሎች ጠቅላይ መምሪያዎች ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍና ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።
የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ጉብኝቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የከፍተኛ አመራሩ የሥራ ጉብኝት ለክፍሉ አባላት ትልቅ የሞራል ጥንካሬ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
ተቋሙ ህዝባዊ አመኔታውን አጠናክሮ ለመቀጠል እና መረጃዎችን በጥራት ለህዝብ ለማድረስ የተጀመሩትን ዘመናዊ የኮሚዩኒኬሽን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አረጋግጠዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ አክለውም ተቋሙ ከኮሚዩኒኬሽን ሥራው ጎን ለጎን የወንጀል መከላከል እና የሕግ ማስከበር ተግባራቱን በላቀ ቁርጠኝነት እያከናወነ ይገኛል።
የወንጀል ስጋቶችን አስቀድሞ ለመግታት በህብረተሰብ አቀፍ ፖሊስ አሰራር የታገዘ የመከላከል ስራ መጠናከሩን ጠቁመው፣ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ደግሞ በሳይንሳዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የሙያ ብቃት በመጠቀም በጥራት እና በፈጣን ሁኔታ የመርመር አቅም ማደጉን ገልጸዋል።
ህዝቡ ለፖሊስ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ በማቅረብ የሰላም እና የደህንነት ማስከበር ስራው በከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚቀጥል ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ አረጋግጠዋል።






