ሌተናል ጄነራል ጥጋቡ ይልማ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አቀባበል ተደረገላቸው

ሌተናል ጄነራል ጥጋቡ ይልማ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አቀባበል ተደረገላቸው

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው የተሾሙት ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ በዋና ጠቅላይ መምሪያው ማኔጅመንት አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

አዲሱ አዛዥ ወደ ኃላፊነት በመጡበት ወቅት ከተቋሙ የቀድሞ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ጋር ይፋዊ የሥራ ርክክብ ፈጽመዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ባለፉት ጊዜያት ከክልሉ ፖሊስ ሰራዊት ጋር በመሆን የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል። የፖሊስ ተቋሙን በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ ለማዘመን ጥረት አድርገናል፣ ለዚህም ሁሉም የማኔጅመንት አባላትና የሰራዊቱ አባላት ላደረጉት ድጋፍ አመሰግናለሁ ብለዋል።

አዲሱ አዛዥም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉና የክልሉን ፖሊስ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩት ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም አክለው ተናግረዋል።

በመቀጠልም ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ ከዋና ጠቅላይ መምሪያው የማኔጅመንት አመራሮች እንዲሁም ከዋና መምሪያ፣ ከመምሪያ እና ከዋና ክፍል አመራሮች ጋር በነበራቸው የመጀመሪያ የሥራ ውይይትና ትውውቅ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚከናወኑ የጸጥታና ሕግ ማስከበር ሥራዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ መኮንኖች በበኩላቸው ለአዲሱ አዛዥ የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት በማስተላለፍ በተቋሙ ውስጥ ስላሉ የጸጥታ ሁኔታዎችና የስራ አፈፃፀም አጭር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አክለውም የተቋሙን ራዕይ ለማሳካትና የክልሉን ህዝብ ሰላም ለማረጋገጥ ከአዲሱ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጋር ተቀናጅተው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ የቴክኖሎጂና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን የወንጀል መከላከልና የመረጃ አደረጃጀት ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍ የሕዝቡን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

በማጠቃለያም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የፖሊስ ተቋሙን ህዝባዊና ዘመናዊ አገልግሎት የማጠናከር ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንሰራለን። ለዚህም የሁላችንም ትብብርና ርብርብ ያስፈልጋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top