የ2019 በጀት ዓመት የወንጀል መከላከል ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ከአመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የወንጀል ስጋቶችን በቅድመ-መከላከል ተግባራት ለማክሸፍ እና የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የተቀናጀ አሠራር ይዘረጋል።
የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዳችን ዋና ትኩረት ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ከመከታተል ይልቅ እንዳይፈጸም የሚያስችሉ የቅድመ-መከላከል ስልቶችን በላቀ ደረጃ መተግበር ነው” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ለዚህም የኅብረተሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን (Community Policing) በማጠናከር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ቅንጅት እና መረጃ የመለዋወጥ አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዕቅድ ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የፖሊስ አባላትና አመራሮች በበኩላቸው የቀረበው ዕቅድ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና የወንጀል ስጋቶችን በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ለመግታት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዕቅዱ የፖሊስ ሰራዊቱን የውጊያና የሙያ ብቃት ከማሳደግ ባለፈ ከሕዝቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን በወቅቱ በመተንተን ወንጀልን በቅድመ-መከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል መከላከል ሥርዓት መዘርጋት፣ የፖሊስን ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም ማሳደግ እና ከሌሎች የፍትሕና ጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል።
ተሳታፊዎቹ የተጣለባቸውን ግዴታ በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ የቀረቡ ገንቢ ሀሳቦችን በማካተት ዕቅዱን ወደ ሙሉ ተግባር ለማስገባት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
የምክክር መድረኩ መጠናቀቅን ተከተሎም የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ከስሩ ከሚገኙ አራት ዋና መምሪያዎች ጋር የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ፈጽሟል።










