“ህዝባችን የሚያነሳቸውን የፖሊስ አገልግሎት እና ጥያቄዎች በታማኝነትና በቅንነት ለመመለስ ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚሽነር ጀኔራል ጽሕፈት ቤት፣ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያዎችን እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማን በስኬት አጠናቋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ ተቋሙን ዘመናዊና ወቅቱን የዋጀ ለማድረግ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች፣ የቴክኖሎጂና የህገ-ወጥ ታጣቂ አካላትን የመቆጣጠር ስኬቶች፣ የህግ ማስከበር እንዲሁም የተቋም ግንባታ ውጤቶች በዝርዝር ተገምግመዋል።
የክልሉን ዋና ዋና ከተሞች ሰርገው በመግባት ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ ህገ-ወጥ ታጣቂዎችን የመቆጣጠር፣ የመንግስትና የህዝብ ንብረቶችን የመጠበቅ እንዲሁም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫና አበይት ጣና ፎረም እና አይማኖታዊና መንግስታዊ ፕሮገራሞች ከሌሎች የፀጥታና የደህንነት ተቋም ጋር በመቀናጀት ያለአንዳች የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቁ የማድረግ ስራ ተከናውኗል።
በወንጀል ምርመራና ፎረንሲክ ዘርፍ ከተመዘገቡ ከ19 ሺህ 9 መቶ በላይ የክስ መዝገቦች መካከል ከ15 ሺህ 7 መቶ በላይ የሚሆኑት ተመርምረው ለፍትህ አካላት ተልከዋል።
የጣት አሻራ እና የፎረንሲክ ምርመራዎችን በማዘመን፣ የሙስና እና የመንግስት ንብረት ምዝበራ ወንጀሎችን በማጣራት የህዝብና የመንግስት ሀብት ማዳን ተችሏል።
የሰው ሀብት፣ ሎጀስቲክስ እና የህግ አገልግሎትን በተመለከተ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አያያዝ ስርዓት የተዘረጋ ሲሆን ለአባላት አዲስ የደንብ ልብስና የሎጀስቲክስ አቅርቦቶች ለሰራዊቱ ተደራሽ የማድረግ ስራ በጥንካሬ ተገልፃል ።
በፖሊስ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርስተኢ ኮሌጅ የማሸጋገርና በሰዉ ሀይል በአደረጃጀት ለማደራጀት ሰፊ ጥረት የተደረገ ሲሆን ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕረግ ሽግግር ሥልጠና ሥርዓተ-ትምህርትና ሞጁል ተቀርጾ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ የ1ኛ ዲግሪ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት እና የ4ኛው ዙር ክልል አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በስኬት ተካሂዷል።
የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ፣ የተመዘገቡት ስኬቶች ፖሊስ ከህዝቡና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ትግል የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት በማረም የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው፣ ተቋሙን ተወዳዳሪ ለማድረግና የፍትህ ስርዓቱን ለማቃናት በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመረኮዘ የምርመራ ስራ መስራትና ለውጥ መር አስተሳሰብን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው በበጀት ዓመቱ ከሰው ሀይል ግንባታ፣ ከሪፎርም አፈፃፀም፣ ከበጀት አስተዳደርና ሎጀስቲክ አጠቃቀም አንፃር ተቋሙን የሚያሻግሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የኮሚሽነር ጀኔራል ጽህፈት ቤት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ተቋሙን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገሩና የሰራዊቱን ዝግጁነት ያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የመሠረታዊ ፖሊስ እና ልዩ ልዩ የፖሊስ ሙያ ሥልጠናዎች ከመሰጠታቸው ባሻገር በርካታ ቁጥር ላላቸው የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወቅቱን የዋጀ ሥልጠና መሰጠቱን በሪፖርታቸው አብራርተዋል።
የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው ህብረተሰቡን ከሀሰተኛ መረጃዎች በመጠበቅ ወቅታዊና ታማኝ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ መቻሉ በህዝብ እና በፖሊስ መካከል ያለውን መተማመን ማሳደጉን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር፣ የምስራቅ ጎጃም እንዲሁም የደብረብርሃን እና የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዦች የ2018 በጀት ዐመት ሪፖርት አቅርበዋል።
አዛዦቹ በሪፖርታቸው የፖሊስ ሰራዊቱ የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና የህዝብን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ከፍተኛ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የተጣለበትን የህዝብና የሀገር አደራ በግንባር ቀደምትነት ለመወጣት አሁንም በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከሁሉም የፖሊስ ሰራዊት ጋር የሪፎርም አስፈላጊነት ላይ መተማመን ተደርሶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውሰዋል።
ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር በማስተካከል የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸው የተጠናከረ፣ ያደገ እና አስተማማኝ የጸጥታ ኃይል እየተገነባ እንደሚገኝና ፖሊስን ወደ ቀደመ ቁመናወኡ ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ሁሉም ስትራቴጂክ አመራሮች ቢሮ ላይ ብቻ ሳይሆን ታች ሰራዊቱ ድረስ በመውረድ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አክለውም በጀት ዓመቱ ሪፎርሙ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እና የዲጂታላይዜሽን ስራን ወደ ሁሉም የዞን ፖሊስ መምሪያዎችና ፖሊስ ጣቢያዎች ለማስፋፋት መሰረት የተጣለበት መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ሰብዓዊ መብቱ ተጠብቆለት አገልግሎት እንዲያገኝና ለሰራዊቱ ምቹና ጽዱ የስራ አካባቢ ከመፍጠር አኳያ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን አብራርተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀኔራሉ ገለጻ በ2018 በጀት ዓመት ያጋጠሙንን ዘርፈ-ብዙ የጸጥታ ችግሮችን፣ፈተናዎች ተቋቁመን አበይት ስኬቶችን ማስመዝገብ ችለናል።
ይህ ውጤት የአመራሩና የሙሉ ሰራዊቱ ሙያዊ ጽናት እንዲሁም ከህዝባችንና የጀግናዉ የአገር መከላከያ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር የተደረገው ጠንካራ ቅንጅት ውጤት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በቀጣይ የሪፎርም፣ የዲጂታላይዜሽን እና የተቋም ግንባታ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር እንዲሁም የፖሊስ ሰራዊታችንን ዝግጁነትና ስነ-ምግባር በማሳደግ የክልላችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ አለብን።
“ህዝባችን የሚያነሳቸውን የፍትህና የደህንነት ጥያቄዎች በሳይንሳዊ አሰራር፣ በታማኝነትና በቅንነት ለመመለስ ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል” ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ አመራሮች በበኩላቸው ተቋሙ በትክክለኛ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸው ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና ማኔጅመንታቸዉን እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እዉቅና ሰጥቷል ።
የጀግኖች ማዕከል ግንባታን ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የመጽሐፍ ሽያጭ ገቢን በማበርከት ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ ለኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ምስጋና አቀርቧል።
በተጨማሪም የሠራዊቱ አባላት ደሞዛቸውን በማዋጣት ማዕከሉ እንዲገነባ ያደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ እና አበርክቶ የሚደነቅ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ የፖሊስ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኮሚሽነር ጀኔራሉን አርዓያነት በመከተል ሁሉም የፖሊስ ሰራዊት ቀን ከሌት መስራት እንዳለበት ያመለከቱት ተሳታፊዎቹ በቀጣዩ በጀት ዓመት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግና ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፋት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በኮማንደር ዘመን ዮሐንስ የቀረበ ሲሆን፣ የቀረበውን ዕቅድ መነሻ በማድረግም ኮሚሽነር ጀኔራሉ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
በክልሉ የጸጥታ ኃይል ሰላምና ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ፣ የወንጀል መከላከል አቅምን ማሳደግና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን ማጠናከር፣ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን አቅምና አሰራር ማሻሻል እንዲሁም አጫጭር የስራ ላይ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ሰራዊቱ በስነ-ምግባር የታነጸና ቅን አገልጋይ እንዲሆን ማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።













