ለጥፋት ኃይል ሊተላለፍ የነበረ የጦር መሳሪያ በኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ ተያዘ
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ በተደረገ የተቀናጀ ክትትልና ፍተሻ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ የጦር መሳሪያ፣ የጥይት ካዝና እና የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ ከሶስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።
እንደ ፖሊስ ገለጻ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴው በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማና በተደረገ አፋጣኝ ክትትል ነው።
መነሻቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን ሳይንት ወረዳ ያደረጉት ተጠርጣሪዎቹ መሳሪያውንና አልባሳቱን በቦርከና ክፍለ ከተማ የጎፍ ቀበሌ ልዩ ቦታው ‘እልክብየ’ በተባለው አካባቢ ምሽት 2:30 አካባቢ ሰሌዳ በሌለው ባጃጅ ሲያጓጉዙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
በፍተሻው ወቅትም 9 ታጣፊ የክላሽንኮቭ መሳሪያዎች፣16 የክላሽ ካዝናዎች እና 03 የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብሶች (ዩኒፎርሞች) ተይዘዋል።
በድርጊቱ የተጠረጠሩት ጥላሁን ጌታ አድማሱ፣ መኮንን ካሳ ደምሴ እና ሲሳይ ወርቄ የተባሉ ግለሰቦች የተያዙትን እቃዎች ለጠላት ኃይል አሳልፈው ለመስጠት ሲያጓጉዙ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው አስፈላጊው የፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ያሳየውን ቀናኢነትና ያደረገውን ጥቆማ አመስግኖ መሰል ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በመታገል በኩል የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።




