የፖሊስ የሪፎርም ስኬቶች እና የሕግ ማስከበር አፈጻጸም!
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት፣ 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን የፖሊስ የሪፎርም ስኬቶች እና የሕግ ማስከበር አፈጻጸም በሪፖርት ተመላክቷል።
በጉባኤ ላይ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ሰላምን ለማጽናት፣ የፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰፊና ተስፋ ሰጪ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ያከናወነው አጠቃላይ የሪፎርም ሥራ የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ ተቋሙን ወደ ቀድሞ ክብርና ዝናው እየመለሰው ይገኛል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ የፖሊስ ተቋሙን ምቹ የሥራ አካባቢ የማድረግ፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀም እና አሰራሮችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ተግባራት በአመርቂ ደረጃ መከናወናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የፖሊስ ሠራዊቱ የሙያ ሥነ-ምግባርን ተላብሶ የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጥ በርካታ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን፤ ከፍትሕ ተቋማት፣ ከፌደራል እና ከሌሎች የክልል የጸጥታ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም ለማረጋገጥ የፖሊስ ሠራዊቱ ቀን ከሌት በመሥራት የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ ጀግና ኃይል መሆኑ በጉባኤው ተነስቷል።
ፖሊስ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እና የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለመከላከል ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ውጤት ማስመዝገቡ ተጠቅሷል።
ሰብአዊ መብቶችን ባከበረና ባስከበረ መልኩ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር፣ ወንጀልን የመቀነስ እና ክልሉን ሰላማዊ የማድረግ ሥራዎች ስኬታማ እንደነበሩም ተገልጿል። በተለይም በክልሉ የተከናወኑ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የፖሊስ ሚና የጎላ ነበር።
በበጀት ዓመቱ የወንጀል ምርመራ አቅምን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ቁጥራዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የምርመራ አቅም 83% እንዲሁም የምርመራ ጥራት 85.5% የደረሰ ሲሆን የፎረንሲክ ምርመራ ጥራት 100% መድረሱ በሪፖርቱ ተረጋግጧል።
የቀረቡ 1,558 የሙስና ወንጀል ምርመራ መዛግብት መካከል 1,373ቱ (84%) ምርመራቸው ተጠናቆ ለአቃቤ ሕግ መላካቸው ተመላክቷል።
በዚህም በ87 መዛግብት የተመዘገበ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ማስመለስ የተቻለ ሲሆን ከ3.2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ የመንግሥት መሬትም ተመልሷል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የፖሊስ ተቋሙ ያከናወነው የሪፎርም ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ተቋሙ ወደ ቀድሞ ክብርና ዝናው እየተመለሰ መምጣቱን በጥሩ ሁኔታ አንስተዋል።
አባላቱ አክለውም የፖሊስ ሠራዊቱ የሕዝብንና የሀገርን ደኅንነት ለማስከበር ቀን ከሌት የሚያደርገውን ጥረትና የሚከፍለውን የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት አድንቀዋል።
ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ኮንትሮባንድን በመከላከል፣ ወንጀልን በመቀነስ እንዲሁም በክልሉ የተካሄዱ ሀገራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ባደረገው የጎላ ሚና የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በመጨረሻም “በክልሉ ለተመዘገበው አጠቃላይ የሰላምና የፍትሕ ስኬት የጸጥታ ኃይሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው” ሲሉ አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር በሪፖርታቸው እውቅና ሰጥተዋል።





