በኢትዮዽያ የቻይና ኢምባሲ ልዑካን ቡድን በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሥራ ጉብኝትና ውይይት አከናወኑ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ( ዶ/ር) ዘላለም መንግሥቴ እና ማኔጅመንቱ ከቻይና ኢምባሰሲ በMr SUN Mingxi ምክትል ሚሲዩን መሪ የሚመራ እና የፖሊስ አታሼን ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉት ልዑካን ባህርዳር ሲደርሱ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አቀባበል ተደረጎላቸዋል።
ልዑካኑ ቡድኑም የዋና ጠቅላይ መምሪያውን ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን በላቀ ዝግጅት በተከናወነው በዚህ የስራ ጉብኝት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ በነበረው የምክክር መድረክ አመራሮቹ በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ኃይል ግንባታና ስልጠና፣ በኮሚዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም የዘመኑን ቴክኖሎጂ አሰራር ከማስፋፋት አኳያ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊና ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ እንደገለጹት የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የሁለቱን ወገኖች የቆየ ወዳጅነት ወደ ላቀ የሙያና የቴክኖሎጂ ትብብር የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በመግለጫቸው የቻይና መንግስት እና ህዝብ ከአኢትዬዽያ መንግስትና ህዝብ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን የቻይና መንግስት ለጸጥታ አካላት የሚሰጡት ድጋፍ በፌደራል ፖሊስ በኩል እና በቀጥታ የክልሉ ፖሊስም ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የክልሉ ፖሊስ ከቻይና ፖሊስ ጋር የሚያደርጉት ልዩ ልዩ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል።
የሰለጠነና በቴክኖሎጂ የዳበረ የሰው ኃይል መገንባት ለአንድ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም መሰረት ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ከቻይና ልዑካን ቡድን ጋር ባደረግነው ምክክር የፖሊስ አባላቶቻችንን አቅም ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትና በኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ የሙያ ትብብር ማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ውይይት አካሂደናል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
የተደረገው ውይይት ወደ ተግባር የሚቀየርበት ግልጽ አቅጣጫ መቀመጡንና በቀጣይም የሁለቱ ወገኖች አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ረዳት ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።













