የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገመገመ።
በግምገማ መድረኩ የዋና ጠቅላይ መምሪያው የኮሚሽነር ጀኔራል ጽሕፈት ቤት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀ የዓመቱን አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ማኅበረሰቡ በየአካባቢው በሙሉ ነጻነትና በራስ መተማመን እንዲንቀሳቀስ አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን፣ የእገታ ወንጀሎችንና የመንገድ ላይ ዘረፋዎችን በልዩ ትኩረት ለመግታት የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች ተዳሰዋል።
በተጨማሪም የትራፊክ ቁጥጥርና የክትትል ሥርዓቱን በማጠናከር የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመትን ቀድሞ ለመከላከል የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ተመልክተዋል።
በመድረኩ የዋና ጠቅላይ መምሪያው አመራሮች ባቀረቡት ማብራሪያ በተቋሙ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ መሠረት ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዙ የሲሲቲቪ (CCTV) ካሜራዎችን የመትከል፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን (ዲጂታላይዜሽን) በማጠናከር የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን ወደ ሥራ የማስገባት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ለማጠናከርና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሠራሮችና የሠራዊቱን የደንብ ልብስ ጥያቄዎች የመመለስ ሥራዎች መከናወናቸው የፖሊስን ዲሲፕሊንና ሥነ-ምግባር ወደ ቀድሞ ክብሩና ሞገሱ እንዲመለስ ማድረጉንም አክለው ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ መሠረት በማድረግ ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የፖሊስ ተቋም ዋና የሕግ ማስከበር ተግባሩን እየተወጣ ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል መስዋዕትነት እየከፈለ አዎንታዊ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ ከፍትሕና ከአጋር አካላት ጋር በተደረጉ ቅንጅታዊ ሥራዎች፣ በሪፎርም አፈጻጸም እንዲሁም የ7ኛውን አገራዊ ምርጫ በሰላም በማስጨረስ በኩል የተከናወኑ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ መመራታቸውን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ለቀጣይ የሥራ አቅጣጫ የሚሆኑ አስፈላጊ ግብዓቶችንና አስተያየቶችን የሰጠ ሲሆን የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን የበለጠ ማረጋገጥ፣ ግድያ፣ ዘረፋና እገታ ወንጀሎችን የመቆጣጠር ሥራዎችን ማጠናከር የሚሉ ይገኙበታል።
በተጨማሪም የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ሕዝቡን በስፋት ማሳተፍ፣ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ከፍትሕ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት ማሳደግ እንዲሁም የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች አጠናክሮ ማስተዋወቅ እንደሚገባ አሳስቧል።
የዋና ጠቅላይ መምሪያው አመራሮች በበኩላቸው ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡትን አቅጣጫዎችና ግብዓቶች መሠረት በማድረግ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።





