በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የፖሊስ ተቋማት ማሻሻያ እና የሪፎርም ስራዎች የመስክ ምልከታ ተካሄደ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በከሚሴ ከተማ በመገኘት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፖሊስ መምሪያ እና በከሚሴ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የተቋም ግንባታ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ተጀምሮ የተቋረጠውን የቢሮ ግንባታ በአዲስ መልክ እንደገና ለማስጀመር እንዲሁም ዘመኑን በዋጀ መልኩ እና በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ዋና ጠቅላይ መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኮሚሽነር ጀኔራሉ በጉብኝታቸው ወቅት ገልጸዋል።
የሕንጻ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ተቋሙ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመልክቷል።
በተጨማሪም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ሕንጻ ዘመናዊ የዲጂታይዜሽን አሠራርን ያካተተ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ቢሮውን በማደስ እና ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ በማድረግ ረገድ ያከናወናቸው ሥራዎች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ በከተማው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የተከናወነው የቢሮ እድሳትና ማሻሻያ ሥራ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ውጤታማ የፖሊስ ሪፎርም ማካሄዱን በግልጽ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ዞኑ ከፖሊስ ሰራዊቱ ጎን በመቆም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የፖሊስ ተቋማት መሰረተ ልማት መሻሻል ለፖሊስ አባላት የሥራ መንፈስ መነቃቃት ብቻ ሳይሆን ለሕዝባችን የምንሰጠውን የአገልግሎት ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም የፖሊስ ሰራዊቱ ከተማውንና ዞኑን ከአስከፊ ወንጀሎች በመጠበቅ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የዞኑና የከተማው የፖሊስ አመራሮች እና አባላት በበኩላቸው እየተካሄደ ያለው የተቋም ግንባታና ለሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነት በሙሉ ኃይላቸውና ቁርጠኝነታቸው ህዝብን ለማገልገል የሚያስችላቸው መሆኑን በመግለጽ የተጣለባቸውን የህዝብ ጥበቃና የሕግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በስልጠና ምዕራፍ ላይ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎችን በአካል በመገኘትና በመጎብኘት ከፍተኛ የሞራል እና የማበረታቻ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጉብኝቱ ወቅት እንደተገለጹት ሰልጣኞቹ ያሳዩት ከፍተኛ የዲሲፕሊን፣ የጽናት እና የቁርጠኝነት ደረጃ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
የሀገርን ሰላም፣ ደህንነት እና የሕዝብን አብሮነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የጸጥታ ኃይሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተስመረቶበታል።
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው የተሰጣቸውን ስልጠና እና የተላለፈላቸውን ሀገራዊ አደራ መሰረት በማድረግ የተቀበሉትን ኃላፊነት በከፍተኛ ታማኝነት እና በሙሉ ዝግጁነት ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።










