“በለበስነው የደምብ ልብስና ማዕረግ ልክ ህዝብን ማገልገል ይጠበቅብናል!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)

“በለበስነው የደምብ ልብስና ማዕረግ ልክ ህዝብን ማገልገል ይጠበቅብናል!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በመገኘት ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ አመራሮች እና የፖሊስ አባላት ጋር በሰላምና ጸጥታ፣ በአሰራር ማሻሻያዎች እንዲሁም በሰራዊቱ አቅም ግንባታ ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ወቅት የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አመራሮች እና አባላት በአማራ ክልል ፖሊስ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በተቋማችን ትልቅ ተስፋ እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

በተለይም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ የሚያደርጉት የሰራዊት ግንባታ ሂደት ሰራዊቱ ቆራጥ እና መስዋዕትነት የማይፈራ እንዲሆን ማድረጉን በመጥቀስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ ክብርና ምስጋና አቅርበዋል።

ቀጠናውን ከህገወጥ ታጣቂ ቡድኖች የጸዳና ሰላማዊ ለማድረግ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመራሮቹ አክለዋል።

ጥራቱን የጠበቀ የፖሊስ ደምብ ልብስ በወቅቱ ማቅረብ መቻሉንና የፖሊስን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ስራዎችን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተደረጉ ጥረቶችንም አድናቀዋል።

በተጨማሪም የህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ቀን ከሌት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው ሰራዊት ጥቅማጥቅሞች እንዲከበሩ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰራዊቱን የመኖሪያና የስራ ቦታ ሁኔታዎች የበለጠ ማሻሻል፣ ቀጣይነት ያለው የስልጠና እድሎችን ማመቻቸት እና ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት (Community Policing) ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተውበታል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው ሰራዊቱ መስዋዕትነት ለመክፈል የማያመነታ በመሆኑ አካባቢው ሰላም መሆን መቻሉን ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በጠላት ላይ የበላይነት እየወሰደ ሰላምን እያጸና እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በፖሊስ ሰራዊቱ እና በተቋሙ ውስጥ የተደረገው ሪፎርም በዞኑ ደረጃም ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን ተናግረዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡመር መሀመድ የዞኑ ፖሊስ ሰራዊት የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ አብራርተዋል።

በራስ አቅም ጠላትን መምታት መቻሉን የጠቀሱት አዛዡ የተገኙ ስኬቶች በሙሉ የሰራዊቱ ጽናትና ከሌሎች የደህንነት አካላት ጋር የተደረገ የተቀናጀ ስራ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የቀረቡት የቁሳቁስና የጥቅማጥቅም ማሻሻያዎች የሰራዊቱን የስራ ተነሳሽነት በእጅጉ እንዳደሱት ያመላከቱት ዋና ኢንስፔክተር ኡመር በቀጣይ የሰው ኃይል አያያዝን ማስተካከል እንደሚያስፈልግና ያለውን የአመራር እጥረት ለመቅረፍ ስልጠናዎች ተመቻችተው ክፍተቱ ቢሞላ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ፖሊሳዊ ዲስፕሊን እንዲከበር መደረጉ ሪፎርሙ ካስገኘው ዋና ዋና ውጤቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሰራዊቱ በላቀ ወታደራዊና ፖሊሳዊ ዲስፕሊን የሚከበር እንዲሆን በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው በፖሊስ፣ በመከላከያ ሰራዊት፣ በሚሊሻ አባላትና በሌሎች የደህንነት መዋቅሮች መካከል ያለው ቅንጅት አካባቢውን ከህገወጥ ታጣቂዎች በማጽዳት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ለተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ህገወጥነትንና ህገወጥ ታጣቂዎችን ስርዓት ማስያዝ የፖሊስ ዋነኛ ተግባር መሆኑን አስምረውበታል።

የፖሊስ አባላትን ጥቅማጥቅም ማስከበር፣ የስራ ሁኔታዎችን ማሻሻል፣ በወቅቱ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እና ፖሊሳዊ ዲስፕሊን እንዲከበር ማድረግ የዋና ጠቅላይ መምሪያው ቀዳሚ ትኩረት እንደሆነና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

“በለበስነው የደምብ ልብስና ማዕረግ ልክ ህዝብን ማገልገል ይጠበቅብናል” ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም የሰራዊቱን አቅም በማሳደግ አካባቢውን ከህገወጥ ታጣቂዎች የመጠበቅ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፖሊስ ወቅቱን የጠበቀ በሙያና በስነ-ምግባር የታነጸ እንዲሁም የህዝብ አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን የተጀመረው የሪፎርም ስራ ሳይቋረጥ እንደሚቀጥል በመግለጽ የዞኑ የጸጥታ መዋቅር፣ የአካባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰቡ የጀመሩትን የተቀናጀ የሰላም ማስከበር ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ በመስጠት ውይይቱን አጠናቀዋል።

ለኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ የደዋ ጨፋ ወረዳ ወለዲ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል በማድረግ የባንዲራ ስጦታ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በኩል የተበረከተላቸው ሲሆን ኮሚሽነር ጀኔራሉም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top