“ፖሊስነት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ነው!!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)

“ፖሊስነት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ነው!!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በምስራቅ ጎጃም ዞን እና በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች በመገኘት ከየመምሪያዎቹ አመራሮች (ማኔጅመንት) ጋር ፍሬያማና ስትራቴጂካዊ ውይይት አካሂደዋል።

ጉብኝቱ በአካባቢው ያለውን የፀጥታና የህግ ማስከበር ስራ ይበልጥ ለማጠናከር እና ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የፖሊስ አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ ያለመ ነው።

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ከሙስና የጠራ አገልግሎት ለመስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት “ፖሊስነት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ነው!” ብለዋል።

ህዝባችን ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት የማግኘት ሙሉ መብት አለው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ይህንን መብት ማክበርና ማስከበር ደግሞ የኛ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ቀዳሚ ግዴታ ነው ሲሉ አክለዋል።

አመራሩ ምቹ የስራ ሁኔታን ከመፍጠርና አባላቱን በስነ-ምግባር አንጾ ከማሰማራት አንጻር እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቀልጣፋ እና ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ የስራ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር ለምታደርጉት የሚደነቅ ጥረት የዋና ጠቅላይ መምሪያው ሁለንተናዊ ድጋፍ አይለያችሁም፤ የጀመራችሁትን በጎ ጅምር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራሉ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የምስራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አመራሮች በበኩላቸው የዋና ጠቅላይ መምሪያው ከፍተኛ አመራሮች በቦታው ድረስ መጥተው ስራቸውን በመገምገማቸውና አቅጣጫ በማስቀመጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የተሰጡንን ስልታዊ መመሪያዎች መነሻ በማድረግ የአካባቢያችንን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር ያለንን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት (Community Policing) ግንኙነት ይበልጥ እናጠናክራለን ብለዋል።

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አመራሮች በበኩላቸው የከተማዋን ነዋሪዎችና እንግዶች ደህንነት ለመጠበቅ የምናደርገውን የሌሊትና ቀንን የፓትሮል እንዲሁም የወንጀል መከላከል ስራን በህዝብ ተሳትፎ በመታገዝ አገልጋይነታችንን በተግባር የምናረጋግጥበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ቃላቸውን አድሰዋል።

በዚህ የስራ ጉብኝትና የመስክ ምልከታ ላይ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት፣ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ፣ ኮማንደር ልጅአዱኛ ሙሉጌታ የአድማ መከላከል ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ተገኝተዋል።

በመጨረሻም ኮሚሽነር ጀኔራሉ እና ስትራቴጂክ አመራሮች ከዞኖች አመራሮች ጋር ያደረጉት የሞራል ግንባታ ውይይት እና ጉብኝቱ የዞኑንና የከተማ አስተዳደሩን የፖሊስ ሰራዊት ይበልጥ ያነቃቃና ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top