“የክልሉን ፖሊስ ሰራዊት በዕውቀትና በክህሎት የሚገነባ ዘመናዊ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በትጋት መሥራት ይገባል!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በደብረማርቆስ ከተማ በመገኘት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ያካሄዱ ሲሆን ተቋማዊ አቅምን ለመገንባትና የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ወደፊት በሚያከናውናቸው ስትራቴጅካዊ ስራዎች እና ተቋማዊ ውጤታማነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ እየተተገበሩ ስላሉ የሪፎርም (የለውጥ) ስራዎች ላይ በሰፊው ተመክሯል።
የሪፎርም ስራዎችን ይበልጥ ፍሬያማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በውይይቱ ላይ የጋራ መግባባትና አቅጣጫዎች መቀመጣቸው ታውቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ባቀረቡት ሪፖርት ተቋሙ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም ሆኖ በርካታ ፖሊሳዊ ስልጠናዎችን በስኬት ማከናወኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት አክለውም ተቋሙ ከደረሰበት ውድመት በፍጥነት አገግሞ ዛሬ ላይ ወደቆመበት ተቋማዊ አቋም እንዲመለስ የኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ሁለንተናዊ ድጋፍና የቅርብ ክትትል እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ይህ ውድመት ተቋሙን ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎት እንዳይቀር የተደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ታሪካዊና ምንጊዜም በኩራት የሚታወስ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዋና ጠቅላይ መምሪያው እገዛና የአመራሩ ቁርጠኝነት ለእኛ ትልቅ ሞራልና የውስጥ ጉልበት ሆኖናል ያሉት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች ከግቡ ለማድረስና ተቋማዊ ተልዕኮን በላቀ ደረጃ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍና የኮሚሽነር ጀኔራሉ ማበረታቻ ለስራቸው ትልቅ ተነሳሽነት መፍጠሩን አብራርተዋል።
የተደረገልን የቅርብ ድጋፍ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንድንሻገር የውስጥ አቅም ሆኖናል ያሉት ተወያይ አመራሮች በቀጣይ የተጣለብንን ህዝባዊና መንግስታዊ አደራን ለመወጣትና የጀመርናቸውን የሪፎርም ስራዎች ስኬታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፈተናዎችና ውድመቶች የጉዟችን መሰናክሎች እንጂ የዓላማችን ማቆሚያ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ገለጻ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የደረሰበትን ከባድ ፈተና ተቋቁሞ ለአባላትና አመራሮች በርካታ ስልጠናዎችን በስኬት ማጠናቀቁ ተቋማዊ ጥንካሬያችንን እና የማይበገረውን የፖሊስ ሰራዊታችንን ወታደራዊ ስነ-ልቦና በተግባር ያሳየበት ነው።
ፖሊስነት በስሜት የሚመራ ሳይሆን በሰለጠነ አእምሮ፣ በዳበረ ክህሎትና በህግ የበላይነት ላይ የሚቆም ሙያ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) “ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የክልሉን ፖሊስ ሰራዊት በዕውቀትና በክህሎት የሚገነባ ዘመናዊ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በትጋት መሥራት ይገባል!” ሲሉ አስታውቀዋል።
የፖሊስ ሪፎርም በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሰረተ የሰው ኃይል መገንባትን ይጠይቃል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ እድገትና ስኬት እንዲያስመዘግብ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሁለንተናዊ ድጋፉንና የቅርብ ክትትሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አመራርና አባላት የምንጠብቀውም ተልዕኮን በላቀ ዲስፕሊንና በቁርጠኝነት መወጣትን ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አመራርና አባላትም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ስሜት በማስፈጸም የክልሉን ፖሊስ ሰራዊት በዕውቀትና በክህሎት የሚገነባ ዘመናዊ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በትጋት መሥራት እንዳለባቸው ኮሚሽነር ጀኔራሉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሪፎርም ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የፖሊስ ኃይሉን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግና በዕውቀት የዳበረ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።


















