የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸሙን የገመገመበትና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ያደረገበት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ የወንጀል ምርመራዎች ጎን ለጎን፣ ከወቅታዊ የፀጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወንጀሎችን የመመርመር፣ ከወረዳና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የአሻራ ምርመራ የማከናወን እንዲሁም ህገወጥ የመሬት ወረራና የመንግስት ንብረት ምዝበራ መዝገቦችን የማጣራት ስራዎች ተከናውነዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌዉ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ እንደገለጹት፣ በተገባደደው በጀት ዓመት ከ19ሺህ 9መቶ በላይ የክስ መዝገቦች ቀርበው ከ15ሺህ 7መቶ በላይ መዝገቦች ላይ ምርመራ ተጣርቶ ለሚመለከተው የፍትህ አካል መላኩን ገልፀዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌዉ ገለጻ፣ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የተሰራው የምርመራ ስራ ይበል የሚያሰኝ እና ለቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ እርሾ የሚጥል ነው ብለዋል።

የወንጀል ምርመራ ስራ ለፍትህ ስርዓቱ መጎልበትና ለህዝባችን የፍትህ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌዉ በተሰጠን ሙያ እና ሃላፊነት ልክ ማህበረሰባችንን በእኩልነት፣በፍትሂዊነት፣በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንደሚያስፈልም አሳስበዋል።

ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና የፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራትና በአጥፊዎች ላይ ጠንከር ያለ የምርመራ ስራ በማከናወን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ የህዝብን የፍትህ ጥያቄ የሚመልሱ የወንጀል ምርመራ ስራን መስራት እንደሚገባም ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመትም የምርመራ አቅምን በማሳደግና በማዘመን የፍትህ ስርዓቱን ለማቃናትና ተቋሙን ተወዳዳሪ ለማድረግ በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ውጤታማ ስራን መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው መልክት አስተላልፈዋል ።

የጠቅላይ መምሪያው የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደጀን ወዳጅ በበኩላቸው በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት በክልል ደረጃ የተከናወኑ የዕገታ፣የግዲያ እና መሰል ወንጀሎች የምርመራ ስራ አመርቂ እንደነበሩ ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የምርመራ ስራዎች የመመርመር አቅምን ከፍ ያደረጉ በመሆናቸው ከ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡንም ኮማንደሩ አክለዋል።

ኮማንደር መካሽ ተክለ ብርሃንየጠቅላይ መምሪያው የፎረንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተደረጉ የጣት አሻራ ምርመራና ሌሎች የምርመራ ስራዎች ጥፋተኛን ተገቢውን የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጠው ያደረጉና የምርመራ ጥራትን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም የፎረንሲክ ምርመራ የምርመራ ስራን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ እና የመርማሪ ባለሙያን ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ በተቋሙ በኩል የተደረገው የሪፎርም ስራ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ በርካታ የመንግስት ንብረት ምዝበራና የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ቀላል የማይባል የመንግስት ንብረትን የማስመለስ ስራ ተሰርቷል ያሉት ደግሞ በመሰረታዊ ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አለምነሽ መለሰ ናቸው።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰሩ ስራዎች አመርቂ እንደነበሩ በመጠቆም ለቀጣይ በጀት ዓመት ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ስራን ለመከወን ሁሉም በየዘርፉ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከር እና ክፍተቶችን በማረም ለወደፊቱ ፍትህን ለሚሻው ማህበረሰብ በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top