በህዝብ ተሳትፎ የተገነባ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማዕከል ተመረቀ

በህዝብ ተሳትፎ የተገነባ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማዕከል ተመረቀ

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ቦርከና ክፍለ ከተማ የየጎፍ ቀበሌ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ኦፊሰሮች ቢሮ እና መኖሪያ ቤት ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።

ፕሮጀክቱ የመንግስትንና የህዝብን ትብብር በማቀናጀት ለሰላምና ለልማት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ያሳየበት ነው ተብሏል።

የምረቃ መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሀመድአሚን የሱፍ እንደገለጹት፣ የተገነባው ህንፃ የድንጋይና የኮንክሪት ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ ነዋሪዎች ለሰላማቸውና ለልማታቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባው አክለውም፣ የልማት ስራዎች የህዝብን ድጋፍና ተሳትፎ ሲያገኙ ዘላቂና ውጤታማ እንደሚሆኑ በተግባር መረጋገጡን ጠቁመው፤ ለግንባታው መሳካት በገንዘብ፣ በጉልበትና በሃሳብ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙህዬ በበኩላቸው፣ አዲሱ ግንባታ የፖሊስ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ከመደረጉም ባለፈ፣ የኦፊሰሮችን የስራ ተነሳሽነት በማሳደግ የወንጀል መከላከል ስራውን በእጅጉ እንደሚያቀላጥፈው አስረድተዋል።

ማዕከሉ ለሰላም፣ ለደህንነትና ለፍትህ አገልግሎት መሻሻል የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት በመግለጽ፣ የህዝብና የፖሊስ የጋራ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የቦርከና ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሁሴን ሰይድ፣ ግንባታው በክፍለ ከተማው የተመዘገበ የህዝብ ተሳትፎ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

አመራሩ ከህዝብና ከፖሊስ አባላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሰራው ይህ ስራ፣ ለሌሎች ቀበሌዎችም በአርአያነት የሚወሰድ ተሞክሮ እንደሆነ ገልጸዋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top