የአማራ ክልል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎችን ገመገመ፤ የቴክኖሎጂና የተቋም ግንባታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎችን ገመገመ፤ የቴክኖሎጂና የተቋም ግንባታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።

የኮሚሽነር ጀኔራል ተጠሪ የሆኑ ዋና መምሪያዎች እና መምሪያዎች የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማቸውን በስኬት አጠናቀዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ተቋሙን ዘመናዊና ወቅቱን የዋጀ ለማድረግ የተከናወኑ በርካታ የሪፎርም (Reform) ስራዎች ውጤታማ መሆናቸው ተገልጿል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስና ወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረት ለመፍታት፣ የቆየውን የነበረ አስተሳሰብና አሰራር መቀየር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ባለፈው በጀት ዓመት ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል።

ተቋሙ ያጋጠሙትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተቋቁሞ በማለፍ፣ ለውጡን ማስተናገድ የሚችልና የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከብር ዘመናዊ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች የተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል።

የሰራዊቱን የሥራ ተነሳሽነት ሊያሳድግ የሚችል ዘመናዊ ባለ 7 ወለል የቢሮ ህንፃ ማስፋፊያ ተገንብቷል። የክልሉ መንግስት ባደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ለቢሮው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በስታንዳርዱ እንዲሟሉ በመደረጉ የነበረውን እንግልትና መጉላላት ማስቀረት ተችሏል።

ለወንጀል መከላከልና ለተልዕኮ ማሳኪያ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በታቀደው መሠረት የዘመቻ እና የወንጀል ክትትል ክፍሎች ዝግጁ ተደርገዋል።

ከፌደራል ፖሊስ የተገናኘው የዜጎች የወንጀል መረጃ መስጫ ማዕከል (EFP) መተግበሪያም (App) በስራ ላይ ውሏል።

በየደረጃው ባሉ የኃላፊነት መደቦች ላይ አዳዲስ የአመራር ምደባዎች የተከናወኑ ሲሆን ተቋማዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስታንዳርዶችና ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል።

በተመረጡ የሥልጠና ርዕሶች ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኙ አመራርና አባላት በክላስተር በ5 ቀጠና በመከፈል ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

ተቋሙ ውጤታማ የበጀት ፍላጎት ዕቅድ በማዘጋጀትና በጀትን በአግባቡ በመደልደል ስራ ላይ እንዲውል መደረጉ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ እና ከተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች ተጠቃሾች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የክልሉን ዋና ዋና ከተሞች ሰርገው በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፍጠር የሚሰማሩ የጠላት ኃይሎችንና የህገወጥ ታጣቂ ቡድኑን ተዋጊዎች ተከታትሎ የመያዝ እና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራ ተከናውኗል።

የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ በኩልም ማህበረሰቡና የፖሊስ ሰራዊቱ ከተለያዩ የሀሰትና የተዛቡ መረጃዎች ተጠብቀው እውነታውን እንዲያውቁ ለማድረግ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ታማኝ የሆኑ የፖሊስ መረጃዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች (በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች፣ በህትመት ውጤቶች፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን) ለህዝብና ለሰራዊቱ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

ይህ ፈጣንና ተአማኒ የመረጃ ፍሰት በህዝብና በፖሊስ መካከል ያለውን መተማመን ከማሳደጉም በላይ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና የክልሉን ሰላምና ደህንነት በጋራ ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በሌላ በኩል ከተቋማዊ ገፅታ ግንባታና ከስነ-ልቦና ዝግጁነት አንጻር የፖሊስ ማርች ባንድና ኪነት ቡድን አባላት ደማቅና አርአያነት ያላቸው ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

ቡድኑ በተለያዩ ሀገራዊና ክልላዊ ሁነቶች፣ በስልጠና ማጠናቀቂያ ስነ-ስርዓቶችና በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ሰፊ ስራዎችን ሰርተዋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑም ከአማራ ክልል ፖሊስ ባሻገር የክልሉን እና የሀገራችን ስም በማስጠራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡ በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል።

የጋራ ቅንጅትን በማጠናከር ረገድም ከፍትህ፣ ሚሊሻ፣ ሰላምና ፀጥታ፣ ፍርድ ቤት እና ማረሚያ ቤቶች ጋር በጋራ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፤ ከአጎራባች ክልሎች (አፋር፣ ኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ) ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ላይ የፀጥታ ችግሮች በቅድመ-መከላከል እንዲፈቱ የጋራ ውይይቶች ተደርገዋል።

የኮሚሽነር ጀኔራል ጽህፈት ቤት ዋና መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ኮማንደር ነጋ ድንበሩ በግምገማ መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የጀመርናቸው የሪፎርም ስራዎች ተቋማችንን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገሩና የፖሊስ ሰራዊታችንን ዝግጁነት ያሳደጉ ናቸው ብለዋል።

ያጋጠሙንን የጸጥታ ፈተናዎች ተቋቁመን የህዝባችንን ሰላም ማስከበር የቻልነው በእነዚህ የሪፎርም ስራዎች በፈጠርነው አዲስ አቅም ነው። በቀጣይም የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ አስጠብቆ ማስቀጠልና ስራዎቻችንን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ ኮማንደር ነጋ ድንበሩ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

የኮሚዩኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ታማኝ የሆኑ የፖሊስ መረጃዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለህዝብና ለሰራዊቱ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ችለናል ብለዋል።

ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አክለውም ይህ ተቋማዊ ገፅታን የመገንባትና መረጃን የማጋራት ስራ ህብረተሰቡ የጸጥታ ስጋቶችን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ከፖሊስ ጎን በቁርጠኝነት እንዲቆም ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ሲሉ ገልጸዋል።

የሕግ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሙሉጌታ አያልነህ ባቀረቡት ማብራሪያ ተቋሙ በወንጀልና በፍታብሔር የሚቀርቡበትን ክሶች ጥብቅና በመቆም ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልጸው ተቋሙን ከገንዘብና ከንብረት ብክነት ለመታደግ የተደረጉ የሕግ ክርክሮች ውጤታማ በመሆናቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠር የህዝብና የመንግስት ሀብት ማዳን መቻሉን አብራርተዋል።

በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊ አመራሮች በቀጣይም የተቋሙን የሪፎርም ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን (ዲጂታላይዜሽን) በማሳደግ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት በማስፋት የክልሉን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top